“አስዋንን ግብፅ እንደምታስተዳድር ሁሉ ሕዳሴንም ኢትዮጵያ ታስተዳድራለች”፡ አምባሳደር ዲና
“ሱዳንን ወደነበርንበት እንመለስና ድንበሩን እናካልላለን ብለናታል” ብለዋል ቃል አቀባዩ
ስምምነት የተደረሰባቸውና ያልተደረሰባቸው የድርድር ጉዳዮች ተለይተው ሊቀርቡ መሆኑን አምባሳደሩ ገልጸዋል
የኢትዮጵያ ፣ ሱዳንና ግብፅ ባለሙያዎች ሕዳሴ ግድብ ድርድር ላይ ስምምነት የተደረሰባቸውንና ያልተደረሰባቸውን ጉዳዮች ለይተው ዕሁድ እንዲያቀርቡ መወሰኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።
የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በሰጡት ሳምንታዊ መግለጫ በግድቡ የወደፊት አስተዳደር ላይ ብዥታ እንደሌለና ልክ አስዋን ግድብን ግብፅ እንደምታስተዳድረው ሁሉ ሕዳሴ ግድቡን እና ሌሎች ግድቦችን ኢትዮጵያ ናት የምታስተዳድረው ብለዋል። በዚህ ላይ ትክክል ያልሆኑ ነገሮችን የሚያቀርቡ እንዳሉ የገለጹት አምባሳደር ዲና ምንም ብዥታ ሊፈጠር እንደማይገባ አስታውቀዋል። በጥቅሉ ከ 70 እና 80 በመቶ በላይ በሆነ መንገድ መግባባት መደረሱንም ቃል አቀባዩ አንስተዋል።
የሀገራቱ ባለሙያዎች እስካሁን ስምምነት የተደረሰባቸውና ያልተደረሰባቸውን ጉዳዮች ለይተው ለመጪው ዕሁድ እንዲያቀርቡ የተወሰነ ሲሆን የሱዳን ባለሙዎች ግን ትናንት አለመሳተፋቸው ተገልጿል። በመሆኑም የኢትዮጵና የግብጽ ባለሙዎች የሱዳንን ተወካዮች እየጠበቁ መሆናቸውን ነው አምባሳደር ዲና ያነሱት።
የኢትዮ-ሱዳን ድንበር ጉዳይ
ከሰሞኑ ኢትዮጵያ ከሱዳን በምትዋሰንበት ድንበር ላይ ያለውን ሁኔታ “ሱዳንን ወደነበርንበት እንመለስና ድንበሩን እናካልላለን” ብለናታል ሲሉ ገልጸዋል፡፡
የድንበር ጉዳይ በግርግር ሳይሆን በንግግር እንዲፈታ ኢትዮጵያ ፍላጎት ያላት መሆኑን ለሱዳን አንስተናልም ነው ያሉት። ኢትዮጵያ በሕግ ማስከበር ስራ ላይ በነበረችበት ወቅት እንደዚህ አይነት ነገር ማድረግ ተገቢ እንዳልሆነ ያነሱት ቃል አቀባዩ "ፉከራ አያዋጣም" ሲሉ ተናግረዋል።
ሕዝብ ሉዓላዊነቱን ዝም ብሎ ሜዳ ላይ አይተውም ያሉት አምባሳደር ዲና ችግሩ በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ ፍላጎታችን ነው ብለዋል።