“አምባሳደር ዲና ግብፅን በተመለከተ ኃላፊነት የጎደለው አስተያየት ሰጥተዋል” የግብፅ ውጭ ጉ/ሚ ቃል አቀባይ
“በኢትዮጵያና በጎረቤቶቿ መካከል ግጭት መፍጠር የሚፈልጉ የውጭ ኃይሎች አሉ አልኩ እንጂ ስም አልጠቀስኩም” አምባሳደር ዲና
“ሌባ እናት ልጇን ስለማታምን እኛ ነን ካሉ ምንም ማድረግ አንችልም” አምባሳደር ዲና ሙፍቲ
የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ባለፈው ማክሰኞ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ፣ “የአፍሪካ ቀንድና ምስራቅ አፍሪካ አካባቢ እንዲተራመስ የሚፈልጉ አካላት አሉ” ማለታቸውን ተከትሎ ግብጽ በኩል ቅሬታዎች እየመጡ ነው፡፡ “የሱዳንን ሰፊ መሬትን የያዙ አሉ፤ ግን ለሱዳን ተቆርቋሪ እየመሰሉ ይረብሻሉ” ያሉት ቃል አቀባዩ “ስማቸውን መናገር ግን አልፈልግም ፤ እናንተው ታውቋቸዋላችሁ” ሲሉ ማንነታቸውን በግልጽ ሳይጠቅሱ ማለፋቸው ይታወሳል፡፡
የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ደግሞ ዛሬ ባወጣው መግለጫ “የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ቃል አቀባይ በግብጽ የውስጥ ጉዳይ ላይ አስተያየት መስጠታቸው ተገቢ አይደለም” ብሏል፡፡ “አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ግብጽን በተመለከተ ኃላፊነት የጎደለው አስተያየት ሰጥተዋል” ያሉት የግብፅ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር አሕመድ ሀፊዝ “ግብፅ የግድቡን ግንባታ የምትቃወመው በሀገሪቱ ያለባትን ቀውስ ለማቀዝቀዝ ነው ማለታቸው ተገቢ አስተያየት አይደለም” ሲሉም ነው የገለጹት፡፡
የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በበኩላቸው “እኔ ቀጣናውን የሚረብሹ፤ ኢትዮጵያና ጎረቤቶቿን ማበጣበጥ የሚፈልጉ አካላት አሉ አልኩ እንጂ እከሌ ነው የሚል የሀገር ስም አልጠራሁም” ሲሉ ለአል ዐይን ኒውስ ተናግረዋል፡፡
“በኢትዮጵያና ሱዳን ድንበር አካባቢዎች የሚነሱ ግጭቶች አካባቢውን ማተራመስ በሚፈልጉ የውጭ ኃይሎች ጭምር የተቀነባበሩ ናቸው ያሉት አምባሳደር ዲና እነዚህ አካላት በሱዳን ቢከሽፍባቸው በሌላ ቦታ ሊጀምሩ ይችላሉ” የሚል አስተያየት የሰጡ ቢሆንም ይህንን የሚያደርጉትን አካላት ወይም ሀገር ስም ግን አልጠቀሱም፡፡ “የኢትዮ-ሱዳንን ግንኙነት እንንከባከባለን ፤ ቁማር የሚጫወቱትን ማጋለጥ እንፈልጋለን ፤ ለነዚህ ሰዎች ዕድል አንሰጥም” ያሉት አምባሳደር ዲና “የአፍሪካ ቀንድና ምስራቅ አፍሪካ አካባቢ እንዲተራመስ የሚፈልጉ አካላት አሉ ነው ያልነው ፣ ነገር ግን ሌባ እናት ልጇን ስለማታምን ይህንን የምናደርገው እኛ ነን ካሉ ምንም ማድረግ አንችልም” ብለዋል፡፡
“የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ የግብፅን የውስጥ ጉዳይ በተመለከተ አስተያየት ሰጥተዋል” በሚል የግብፅ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በካይሮ የኢትዮጵያ አምባሳደር ተወካይ ማብራሪያ እንዲሰጡት መጥራቱም ይታወቃል፡፡ ይህን በተመለከተ ለአል ዐይን ሀሳባቸውን የሰጡት አምባሳደር ዲና “በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ማብራሪያ ለመጠየቅ አምባሳደር/ተወካይ መጥራት የተለመደ ነው” ብለዋል፡፡ “ይህ እኛም ልናደርገው የምንችለው ጉዳይ ስለሆነ ሊያነጋግር ሚገባ ጉዳይ አይደለም” ብለዋል፡፡
አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በድጋሚ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ከመሆናቸው በፊት በግብፅ የኢትዮጵያ አምባሳደር ነበሩ።