የኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ አሶሴሽን የብር ኖቶቹን የመለወጡ ሂደት መፋጠን እንዳለበት ገለጸ
የንግድ ባንኮች ከትናንት መስከረም 6/2013 ዓ.ም. ጀምሮ ከብሔራዊ ባንክ ወጪ በማድረግ የብር ኖቶችን መቀየር ጀምረዋል
የብር ኖቶቹን የመለወጡ ሂደት መፋጠን ምን ፋይዳ አለው?
የኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ አሶሴሽን የብር ኖቶቹን የመለወጡ ሂደት መፋጠን እንዳለበት ገለጸ
ነባሮቹን የብር ኖቶች በአዲስ የመለወጡ ስራ ትናንት በተለያዩ ባንኮች መጀመሩ ይታወቃል፡፡ በአጠቃላይ 3.7 ቢሊዮን ብር ወጪ የተደረገበት ከ10 እስከ 200 ብር 2.9 ቢሊዮን የብር ኖት ታትሞ ወደ ሀገር ዉስጥ የገባ ሲሆን ይህም ለተለያዩ ባንኮች ተሰራጭቶ ነው ቅያሪው የተጀመረው፡፡ መንግሥት አብዛኛው የገንዘብ ቅያሪ በ 1 ወር ዉስጥ እንደሚጠናቀቅ ገልጾ አጠቃላይ ሂደቱ ግን በ3 ወራት እንደሚያበቃ አስታውቋል፡፡
ነባሮቹን የብር ኖቶች በአዲስ ለመተካት የሚወስደው ጊዜ መራዘም በኢኮኖሚው ውስጥ የሚዘዋወረውን የገንዘብ መጠን ሊቀንሰው እንደሚችል፣ ሂደቱ ሊፋጠን እንደሚገባ የሚገልጸው፣ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ አሶሴሽን አሳስቧል፡፡ ማህበሩ ባወጣው መግለጫ የብር ኖቶቹን የመለወጡ ሂደት ቢፋጠን የተሻለ እንደሆነና አፋጣኝ የትግበራ እርምጃ ወሳኝ መሆኑን በምክረ ሃሳብነት አቅርቧል፡፡
በብር ኖቶች ለውጥ ይገኛል ተብሎ የሚጠበቀው ሁሉን አቀፍ ጠቀሜታ ሙሉ በሙሉ እውን እንዲሆን ጠንካራ የሕግ መሰረት መዘርጋትና መተግበር አስፈላጊ መሆኑንም ማህበሩ ገልጿል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በቅርቡ በዜጎች እጅ የሚቀመጥ የገንዘብ መጠንን እንዲሁም ከባንክ የሚወጣ የገንዘብ መጠንን ለመወሰን የወሰዳቸው እርምጃዎች አግባብነት እንዳላቸው ያነሳው ማህበሩ የእነዚህንና መሰል መመሪያዎችን አፈጻጻም ማጠናከር ወቅቱ የሚጠይቀው ግዴታ እንደሆነም ነው የገለጸው፡፡
መጠኑ ከፍ ያለ የብር ኖት (ብር 200) በሥራ ላይ እንዲውል መደረጉ ዜጎች በባንኮች በማስቀመጥ ፋንታ በጥሬ ገንዘብ እንዲይዙ የሚያበረታታ ሊሆን እንደሚችል መገንዘብ ተገቢ እንደሆነም ማህበሩ አንስቷል፡፡
ማህበሩ በገጠርና ከመሀል ርቀት ባላቸው አካባቢዎች የሚደረገው የአዲሶቹ የመገበያያ ገንዘቦች ለውጥና ዝውውር ከፍተኛ ጥንቃቄ እንደሚያስፈልገው ያነሳ ሲሆን ነባር የመገበያያ ገንዘቦችን በአዲስ ለመተካት የተወሰደው እርምጃ በአጠቃላይ ኢኮኖሚውም ሆነ በፋይናንስ ዘርፉ እንቅሰቃሴ ላይ የሚኖረው አንደምታ ጉልህ ነውም ብሏል፡፡
በአጭር ጊዜ ሊያጋጥሙ የሚችሉ የብር ኖት ለውጡ ጥቅሞች:-
• የባንክ ተቀማጭ ገንዘብን ብሎም ቁጠባን ሊያሳድግ መቻሉ፤
• የተጭበረበሩ የብር ኖቶችን ከገንዘብ እንቅስቃሴ ማስወገድ ማስቻሉ፤
• ሕጋዊ ያልሆነ የገንዘብ ዝውውርን ከኢኮኖሚው እንቅስቃሴ ማስወገዱ፤
• በታክስ መረቡ የሚታቀፈውን የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ማሳደግ መቻሉ፤
• የባንክ አካውንት የሚኖራቸውን ዜጎች ቁጥር በማሳደግ የባንክ አጠቃቀምን ይበልጥ ተደራሽ ማድረጉ፤
የመካከለኛና የረዥም ጊዜ አጥቅሞች:-
• የታክስ አስተዳደሩን በማሳለጥ የመንግሥት ገቢ እንዲያድግ ያግዛል፤
• የንግድ አሰራሩን በማዘመን የታክስ መሰረትን ያሰፋል፤
• የዋጋ መረጋጋት እንዲኖር ይረዳል፤
• ኢንቨስትመንትን ያሳድጋል፡፡ በዜጎች እጅ በጥሬ ይንቀሳቀስ የነበረ ወይም የተቀመጠ ገንዘብ ወደ ባንኮች እንዲመጣ ያደርጋል፡፡ ይህ ደግሞ ባንኮች ያጋጠማቸውን የብድር ገንዘብ እጥረት በመቅረፍ ለኢንቨስትመንት የሚውል የብድር አቅርቦትን ያሳድጋል፤
• በባንኮች የሚንቀሳቀስ የገንዘብ መጠንን በማሳደግ የገንዘብ ፖሊሲ መሳሪያዎችን አፈጻጸም ውጤታማ እንዲሆኑ ይረዳል፤
• የዲጅታል ፋይናንስ ግብይትና ዝውውር ወቅቱ የሚጠይቀው አሰራር እንደመሆኑ፣ የብር ለውጡ ይህን አሰራር እንዲጎለብት የሚረዳ ነው፡፡ ይህም በጥሬ ገንዘብ ልውውጥ ወቅት የሚከሰት ወጪን በእጅጉ ይቀንሳል የማህበሩ መረጃ እንደሚያትተው፡፡