የገንዘብ ቅያሬው ሂደት የጸጥታ ማስከበር አካላት ከፍተኛ ሚና እየተጫወቱ ይከናወናል ተብሏል
የሚቀየሩ የኢትዮጵያ የብር ኖቶች በአብዛኛው ህትመታቸው መከናወኑ ተገለጸ
የኢትዮጵያ መንግሥት አዳዲስ የደህንነት ገጽታዎች እና ሌሎችም መለያዎች የተካተቱባቸው የገንዘብ ዓይነቶችን ለግብይት እንደሚያውል በዛሬው ዕለት ተገልጿል።
በዚሁ ጉዳይ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ((ዶ/ር) እና የብሔራዊ ባንክ ገዥ ይናገር ደሴ (ዶ/ር) በተገኙበት ዉይይት በመደረግ ላይ ነው፡፡
ነባሮቹ የ10፣ የ50 እና የ100 ብር የገንዘብ ዓይነቶች ሙሉ ለሙሉ እንደሚተኩ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ገልጸዋል።
አዲስ የ200 ብር ገንዘብም በተጨማሪነት ለግልጋሎት ይውላል ነው የተባለው። የ5 ብር ገንዘብ ባለበት ቀጥሎ፣ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ወደ ሣንቲም የሚለወጥ ይሆናል።
ይህ የገንዘብ ቅያሪ መደበኛ ባልሆነ መንገድ እንዲሁም ከፋይናንስ ተቋማት ውጪ የሚዘዋወረውን ገንዘብ ለመሰብሰብ፣ ሙስናን እና የኮንትሮባንድ ሥራዎችን ለመቀልበስ የታለመ እንደሆነ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት በፌስቡክ ገጹ ያወጣው ጽሁፍ ያመለክታል። እርምጃው የፋይናንስ ተቋማት የገንዘብ እጥረትን ለመቋቋም እንዲችሉም እንደሚያግዝ መረጃው ያመለክታል።
በአሁኑ ወቅት አብዛኛው የሕትመት ሥራ ተገባዶ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ግምጃ ቤት ይገኛል። የስርጭት ስርዓት እና ዕቅድ የተዘጋጀ ሲሆን፣ በሚመለከታቸው አካላት አማካኝነት እንደሚተገበርም ጽ/ቤቱ ገልጿል።
በገንዘብ ቅያሬው ሂደት የጸጥታ ማስከበር አካላት ከፍተኛ ሚና የሚጫወቱ ሲሆን፣ የሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ከማኅበረሰቡ ጋር በመተባበር ጥንቃቄ በተሞላበት መንገድ ያስፈጽማሉም ተብሏል።
ከብሔራዊ መከላከያ ሠራዊት፣ ከብሔራዊ የመረጃ እና ደህንነት አገልግሎት እና ከፌደራል ፖሊስ የተውጣጣ ኮማንድ ፖስት ተቋቁሞ፣ ሂደቱን በበላይነት ያስተባብራል። የክልል መንግሥታትም ተመሳሳይ ኮማንድ ፖስት አቋቁመው ሥራውን እንዲያከናውኑም ይጠበቃል።
ኢትዮጵያ ገንዘቧን የሚወክል ምልክት እንዳልነበራት ይታወቃል ያለው መረጃው በቅርቡ ለብር መለያ የሚሆን አዲስ ምልክት ተዘጋጅቶ በጥቅም ላይ ይውላል ሲልም አክሏል።