ጨቅላ ህጻንን ጨምሮ 36 የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች በኦሮሚያ ክልል መገደላቸው ተገለጸ
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን መንግሥት አማኞችን ከጥቃት እንዲጠብቅ ጠይቃለች
የኦሮሚያ ክልል መንግሥት በበኩሉ ጥቃቱ በሸኔ ታጣቂዎች መፈጸሙን ገልጾ እርምጃ እየወድኩ ነው ማለቱ ይታወሳል
ጨቅላ ህጻንን ጨምሮ 36 የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች በኦሮሚያ ክልል መገደላቸው ተገለጸ።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ባወጣችው መግለጫ በኦሮሚያ ክልል በአርሲ ዞን በኦርቶዶክስ ተዋህዶ አማኞች ላይ ያነጣጠረ ጥቃት መፈጸማቸውን ገልጻለች።
ቤተ ክርስቲያኗ ይህን የታቀደ ጥቃት በጥብቅ እንደምታወግዝና የጸጥታ ተቋማትም ምዕመኑን ከጥቃት እንዲከላለሉ ስትል ጠይቃለች።
በቤተ ክርስቲያኗ እንዳለችው ጥቃቶቹ የተፈጸሙት በአርሲ ዞን በሹርካ ወረዳ፣ በሶሌ ሚካኤል፣ በዲገሎ ማርያም፣ በሮቤ እንደቶ ደብረ ምጥማቅ ማርያም አብያተ ክርስቲያናት ላይ በተለያዩ ጊዜያት 36 አማኞች ተገድለዋል።
በዚሁ ጥቃት በሶሌ ዲገሉ እና ጢጆ ለቡ በተባሉ ቀበሌዎች 28 ኦርቶዶክሳዊያን ከየቤታቸው ተለቅመው መገደላቸውን ፤ ከእነዚህ ውስጥ 7ቱ ሴቶችና 21ዱ ወንዶች እንደሆኑ ተገልጿል።
በጥቃቱም እድሜያቸው ከሰባ ዓመት አዛውንት እስከ ሃያ ስምንት ቀን ጨቅላ ሕጻናት እንደሚገኙበት ቤተ ክርስቲያኗ በመግለጫዋ ላይ ጠቅሳለች።
እንዲሁም በዲገሉ ማርያም ቤተክርስቲያን 5 አማኞች ሲገደሉ የሦስት ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን አማኞች ቤት ተቃጥሏል ተብሏል።
ከዚህ ቀደም በሮቤ አንዲቶ ደብረ ምጥማቅ ማርያም ቤተክርስቲያን በዓለ ማርያምን አክብረው ወደ ቤታቸው በመመለስ ላይ የነበሩ 3 ኦርቶዶክሳዊያን ጨለማን ተገን ባደረጉ ነፍሰ ገዳዮች መገደላቸውን ቤተ ክርስቲያኗ አስታውቃለች።
ሆን ተብሎ የቤተ ክርስቲያኗን አማኞችን መግደል ጉዳይ ዕምነትን በነጻነት የማራመድ ህገ መንግስታዊ መብትን የሚጥስ በመሆኑ የጸጥታ ሀይሎች ጥቃቱን እንዲያስቆሙ እና ገዳዮችም ለፍርድ እንዲቀርቡ ቤተ ክርስቲያኗ ጥሪ አቅርባለች።
የኦሮሚያ ክልል መንግሥት በበኩል በአርሲ ዞን ባሉ ወረዳዎች የተፈጸሙት ግድያዎች የሸኔ ታጣቂዎች እንደፈጸሙት ገልጾ መንግሥት ህግ የማስከበር ሀላፊነቱን እንደሚወጣ እና እርምጃ እንደሚወሰድ ገልጿል።