የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ-ክርስቲያን መንግስት አቋሜን ተቀብሏል አለች
ቤተ-ክርስቲያኒቱ የካቲት አምስት ልታደርግ የነበረውን ሰልፍ 'ለተወሰነ' ጊዜ ማራዘሟን ቅዱስ ሲኖዶስ አስታውቋል
ቅዱስ ሲኖዶስ የሰልፍ ማራዘሙ ውሳኔውን የአቋም ለውጥ አይደለም ብሏል
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ-ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ከመንግስት ጋር በተደረገ ውይይት የቤተ-ክርስቲያኒቱን አቋም ቅቡልነት እንዳገኘ አሳውቋል።
መንግስት የቤተ ክርስቲያንን አቋም በመቀበል ወደፊትም የቤተ-ክርስቲያንን አንድነት እና ሉዓላዊነትን በጠበቀ መንገድ እንደሚሠራ ማረጋገጡን ቅዱስ ሲኖዶስ በመግለጫው አረጋግጧል።
በብጹዕ ፓትርያርክ አቡነ ማቲያስ የተመራ 12 ብጹዓን ሉቃነ ጳጳሳት ከጠቅላይ ሚንስትሩና ከመንግስት ከፍተኛ ኃላፊዎች የሀገር ሽማግልዎች በተገኙበት በተካሄደው ስብሰባ፤ የቤተ-ክርስቲያኒቱ አቋም ሙሉ በሙሉ ተቀባይነት አግኝቷል ነው የተባለው።
- የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ከመንግስት ጋር እየተነጋገረች መሆኑን አስታወቀች
- ቤተክርስቲያኗ ካወገዘቻቸው "ቡድኖች" ጋር እኩል መታየቷን ተቃወመች
ቤተ-ክርስቲያን የካቲት አምስት የጠራችው ሀገር አቀፍና ዓለም አቀፍ ሰላማዊ ሰልፍ "ለተወሰነ" ጊዜ እንዲራዘም ቅዱስ ሲኖዶስ መወሰኑን አሳውቋል። ቅዱስ ሲኖዶስ ለውሳኔው የአቋም ለውጥ አድርጌ አይደለም ብሏል።
ለዚህም ሁለት ዐበይት ምክንያቶችን የጠቀሰው ቅዱስ ሲኖዶስ፤ ቤተ-ክርስቲያን አስቀድማ በሮቿን ለሰላም ክፍት በማድረጓ እና በመንግስት በኩል ችግሩን ለመፍታት ፍላጎት በመታየቱ ምክንያት ብቻ መሆኑን እወቁልኝ ብሏል።
ጉዳዩ የአፈጻጸም የድርጊት ጊዜ የሚያስፈልግ በመሆኑ ሰልፉ መራዘሙ ተነግሯል። ነገር ግን መንግሥት የገባውን ቃልና የወሰነውን ውሳኔ የማይፈጽም ከሆነ "መንፈሳዊ ተጋድሏችን ይቀጥላል" ብሏል።
ብጹዓን ሉቃነ ጳጳሳት፣ የሀገረ ስብከት ሠራተኞች፣ አገልጋይ ካህናት እና ምዕመናን በመንግስት እስር፣ ወከባና እንግልት እንደተፈጸመባቸው ቤ-ክርስቲያን ተናግራለች።
መንግስት በአስቸኳይ ከዚህ ድርጊቱ እንዲቆምና የታሠሩትም እንዲፈታ፤ አገልግልታቸውን በሰላምና በነጻነት መስጠት እንዲችሉ ስምምነት ላይ ተደርሷል ነው የተባለው፡፡
የጉዳት ሰለባ ለሆኑቱም መንግስት ተጠርጣሪዎችን ለይቶ በህግ ተጠያቂ እንደሚያደርግ ተስማምቷል።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ-ክርስቲያን በመከራዋ ጊዜ ከጎኗ ለነበሩና ለተሟገቱላት ምስጋናዋንም አቅርባለች። በቅርቡም እውቅና እሰጣለሁ ብላለች።