የኢትዮጵያ የኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ መንግስት በኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን ጉዳይ ጣልቃ እንዳይገባ ጠየቀ
ጉባኤው ችግሩ በራሷ በቤተ-ክርስቲያኒቱ ህግ፣ ቀኖናና ስርዓት ብቻ ተመስርቶ እንዲፈታ መንግስትን አሳስቧል
መንግስት በጉዳዩ ላይ ባሳየው አቋም ከቤተ-ክርስቲያኗ ወቀሳ ገጥሞታል
ስድስት የኃይማኖት ተቋማትን በአባልነት የያዘው የኢትዮጵያ የኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ፤ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን የገጠማት ውስጠ ችግር አሳስቦኛል ብሏል።
የጉባኤው የበላይ ጠባቂ አባላት በሰጡት መግለጫ፥ በቤተ-ክርስቲያኗ ውስጥ የተፈጠረው ችግር በራሷ ህግ፣ ቀኖናና ስርዓት ላይ ብቻ ተመስርቶ እንዲፈታ ጠይቋል።
መንግስት ህገ-መንግስቱን በማክበር በኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ እንዳይገባም ነው ያሳሰበው።
- የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን መንግስትን ከሰሰች
- በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በተፈጠረው ችግር ላይ የመንግስት ምላሽ ምን ይሆናል?
ለዚህም የህገመንግስቱን ኃይማኖትና መንግስት የተለያዩ ናቸው የሚለውን አንቀጽ 11ና የኃይማኖት ነጻነትን የሚደነግገውን አንቀጽ 27ን የጠቀሰው ጉባኤው፤ ይህን ብቻ መሰረት በማድረግ መንግስት እንዲሰራ አሳስቧል።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን "መፈንቅለ ሲኖዶስ" ያለችው የጥር 14ቱ የጳጳሳት ሲመት "መንግስታዊ ሽፋንና እገዛ" እንዳለው ተናግራለች።
ከሰሞኑን የቤተ-ክርስቲያኒቱ አባቶች፣ ሰራተኞችና የእምነቱ ተከታዮች በመንግስት የጸጥታ ኃይሎች እስርና ማዋከብ እንደተፈጸመባቸውም ነው ያስታወቀችው።
መንግስት ህግ እንዲያስከብር የጠየቀችው ቤተ-ክርስቲያን፤ ይልቁንም ላወገዘቻቸው የቀድሞ አባቶች እውቅና እየሰጣቸው መሆኑንም ትከሳለች።
ትናንት በጉዳዩ ላይ መግለጫ የሰጠው የመንግስት ኮሚኒኬሽን አገልግሎት ችግሩ 'በውስጥ አሰራርና ህግ እንዲፈታ' ጠቁሟል።
ቤተክርስቲያኗ የገጠማትን ችግር ተገን በማድግ ግጭት ለመቀስቀስ የሚሰሩ አካላት እንዳሉ ደርሼበታለሁ ያለው መንግስት፤ ህግ የማስከበር ስራ እንደሚሰራም ተናግሯል።
የመግለጫውን ይዘት አስመልክቶ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን ህዝብ ግንኙነት መምሪያ መንግስትንና የያዘውን አቋም የተቸበትን መግለጫ አውጥቷል።
"ቅዱስ ሲኖዶስ በውስጣዊ መንፈሳዊ እና አስተዳደራዊ አሠራሩ የሰጠውን የመጨረሻ ውሳኔ መንግስት ባወጣው መግለጫ አሁንም የማይቀበለው መሆኑን የሚያመለክት ሆኖ አግኝተነዋል" ብሏል።
ቅዳሜ ጥር 27 በሻሸመኔ በርካታ የእምነቱ ተከታዮች በጸጥታ ኃይሎች እንደተገደሉና ከባድ ጉዳት እንደደረሰባቸውም ነው ከቤተክርስቲያኗ የሚወጡ መግለጫዎች የሚያመላክቱት።
ቤተ-ክርስቲያኗ "የአደባባይ ግድያና የህዝብ ፍጅት" ተፈጽሟል ያለች ሲሆን፤ ይህን ድርጊት መንግስት በመግለጫው አለመጥቀሱም አስቆጥቷታል።
"የአደባባይ ግድያና የህዝብ ፍጅት ያልጠቀሰና [መግለጫው] ሀዘኑን እንኳን መግለጽ ያልቻለበትና ያላወገዘ መሆኑን ስንመለከት የመንግስትን ግልጽ ሚና በቀላሉ ለመረዳት እንድንችል ያደርገናል" በማለት ገልጿል።
"ህገ ወጥ" ያላቻቸውን አካላት መንግስት ድጋፍ ከመስጠት እና ልሳን ከመሆን እንዲታቀብም አሳስባለች።