ተወግዘው የነበሩት አባቶች ስምምነቱ ሳይሸራረፍ እንዲተገበር መስማማታቸውን ቤተክርስቲያኗ አስታወቀች
ዛሬ በመንበረ ፓትሪያርክ የተገኙት እነ አቡነ ሳዊሮስ ስምምነቱ ሳይሸራረፍ ይፈጸም ዘንድ እንደሚሰሩ ተናግረዋል
ቤተክርስቲያኗ ትናንት በሰጠችው መግለጫ የካቲት 8 2015 የተደረሰው ስምምነት ተቀግዘው በነበሩት አባቶች ዳግም መጣሱን መግለጿ ይታወሳል
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ተወግዘው የነበሩት አባቶች ዳግም የቤተክርስቲያኗን ቀኗና አክብረው ስምምነቱን ያለምንም መሸራረፍ ለመፈጸም መመለሳቸውን ገልጻለች።
ትናንት ስምምነቱን ጥሰዋል የተባሉት እነ አቡነ ሳዊሮስ በሰጡት መግለጫም ፥ “የካቲት 8 ቀን 2015 የተስማማንባቸውን ዐሥር ነጥቦች ያለመሸራረፍ ለመፈጸም” ዝግጁ ነን ብለዋል።
በቀጣይ የሚከናወኑ ስራዎችንም በቅዱስ ሲኖዶስ አማካኝነት እየተመሩ እንደሚፈጽሙ መስማማታቸውን ነው ያነሱት።
የጠቅላይ ቤተክህነት ስራ አስኪያጅ አቡነ አብርሃምም ስምምነት የተደረሰባቸው 10 ነጥቦች በቅዱስ ሲኖዶሱ ውሳኔ መሰረት እንደሚፈጸሙ ተናግረዋል።
የየካቲት 8ቱ ስምምነት ህገወጥ የተባለውን ሲመት የሰጡ እና የተቀበሉት አባቶች ወደ ቀድሞ የአገልግሎት ቦታቸው እንዲመለሱ እንደሚያደርግ ቤተክርስቲያኗ ገልጻ ነበር።
ይሁን እንጂ ስምምነት ፈጽመው የነበሩት አባቶች “ቀኖና አልጣስንም” የሚል መግለጫ መስጠታቸው ቤተክርስቲያኗ ትናንት “ስምምነቱ ተጥሷል” የሚል መግለጫ እንድትሰጥ አድርጓል።
የጠቅላይ ቤተክህነት ስራ አስኪያጅ አቡነ አብርሃም በመግለጫቸው፥ የጳጳሳቱ ሹመት እንደተጠበቀ ነገር ግን ተሾሙ የተባሉት ኤጲስ ቆጶሳት ሲመት እንደሚሻር ተስማምተን የነበረ ቢሆንም፤ ነገር ግን "ስምምነቱን ገቢራዊ አላደረጉም" ሲሉ ነበር በትናንቱ መግለጫቸው ያነሱት።
ተወግዘው የነበሩት አባቶች ትናንት መግለጫ ሲሰጡ ጵጵስናቸው የተሰረዘባቸው ተሿሚዎች ያልተፈቀዱ አልባሳትን ለብሰው መታየታቸውም "ህግን የጣሰ፤ ስምምነቱን ያፈረሰ" ነው ብለውታል አቡነ አብርሃም።
ሲመተ ጵጵስና አደረግን ያሉ የቀድሞ የቤተክርስቲያኒቱ አባቶች ጥያቄ ከኃይማኖታዊነቱ ይልቅ ፖለቲካዊ ይዘቱ የላቀ ነው ማለታቸውም ይታወሳል።
በዛሬው መግለጫ ግን እነ አቡነ ሳዊሮስ ስለትናንቱ መግለጫቸውም ሆነ ስለተነሳባቸው የስምምነቱን ጥሳችኋል ጉዳይ ማብራሪያን ሳይሰጡ “ስምምነቱን ሳንሸራርፍ እንፈጽማለን” የሚል አጭር መግለጫን በመንበረ ፓትርያርክ ሰጥተዋል።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ጥር 14፣2015 ዓ.ም ሦስት ጳጳሳት በደቡብ ምዕራብ ሽዋ ሀገረስብከት 25 ኤጲስ ቆጶሳት ሾመናል ማለታቸውን ተከትሎ ስርዓቷና ህጓ መጣሱን አሳውቃለች።
ቤተክርስቲያኗ አስቸኳይ የቅዱስ ሲኖዶስ ምላተ ጉባኤ አድርጋም ሲመት የሰጡትን እና የተቀበሉትን በሙሉ ከቤተክርስቲያን እንዲለዩ እና እንዲወገዙ ውሳኔ ማሳለፏ አይዘነጋም።
ተወግዘው የነበሩት አባቶች የካቲት 8 2015 ይቅርታ ጠይቀው 10 ነጥቦች የያዘ ስምምነት ላይ መድረሳቸውም የሚታወስ ነው።