ቤተክርስቲያኗ ተፈጥሮ የነበረውን ችግር በቀኖናው መሰረት መፈታቱን ገለጸች
ከዚህ ቀደም በቅዱስ ሲኖዶስ ተወግዘው የነበሩት ሶስት አባቶችም ወደ ቤተክርስቲያኗ መመለሳቸው ተገልጿል
በሁለቱም ወገን የተወከሉ ብጹአን አባቶች ከሀገር ሽማግሌዎች ጋር መክረው የተደረሰውን ስምምነትም ቅዱስ ሲኖዶሱ ተቀብሎታል ተብሏል
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ተፈጥሮ የነበረው ችግር ቀኖናዊ ስርአቱን ተከትሎ መፈታቱን ቤተክርስቲያኗ አስታወቀች።
ችግሩ በቀኖና ቤተክርስቲያን አማካኝነት መፈታቱንም ብፁዕ የጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ አቡነ አብርሃም በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል።
ከሁለቱም ወገን የተወከሉ ብጹአን አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች ካደረጉት ውይይት በኋላ ችግሩ በቀኖና መሰረት መፈታቱን አቡነ አብረሃም ገልጸዋል።
ቤተክርስቲያኗ ሲኖዶሳዊ አንድነቷ እና ሉአላዊነቷ እንዲከበር ስምምነት መደረሱንም አብራርተዋል።
“መንግስት ፖለቲካዊ ችግሩን በፖለቲካ መንገድ ፤ የቤተክስርሲያን ችግር በቀኖና እንዲፈታ ታልቅ አስተዋጻኦ አድርጓል” ያሉት ብጹዕ አቡነ አብርሃም፥ ለዚህም ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድን አመስግነዋል።
መንግስት ከቤተክርስቲያኗ ጋር ተያይዞ በእስር ላይ የሚገኙ ሰዎችን “ደረጃ በደረጃ እያየ እንደሚለቅ” ጠቅላይ ሚኒስትሩ ማረጋገጣቸውንም ነው ያነሱት።
በመንበረ ፓትሪያርክ በተሰጠው መግለጫ ከዚህ ቀደም በቤተክርስቲያኗ ተወግዘው የነበሩት አባቶችም ተግኝተዋል።
ከመግለጫው አስቀድሞም ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች እና የሀገር ሽማግሌዎች ከብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ጋር ተነጋግረዋል።
ጥር 14፣2015 ሶስት የሀይማኖት አባቶች በደቡብ ምዕራብ ሽዋ ሀገረስበከት ኢጲስቆጶሳት ሾመናል ማለታቸውን ተከትሎ ነበር በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ውስጥ ከባድ የተባለ ችግር የተፈጠረው።
ቤተክርስቲያኗ አስቸኳይ የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባዔ አድርጋ ከቀኖና እና ከስርአተ ቤተክርስቲያን ውጭ ተንቀሳቅሰዋል በማለት ሲመት የሰጡትን እና የተቀበሉትን በሙሉ ከቤተክርስቲያን እንዲለዩ እና እንዲወገዙ ውሳኔ አሳልፋለች።
ቤተክርስቲያኗ መንግስት ጣልቃ በመግባት ላወገዘቻቸው "ቡድኖች" ድጋፍ እየሰጠ ነው ስትል መንግስትን ላይ ጠንካራ ተቃውሞ ማሰማቷም የሚታወስ ነው።
መንግስት ጣልቃ እንዳልገባና ችግሩም በቤተክርስቲያኗ አሰራር እንደሚፈታ ቢገልጽም ቤተክርስቲያኗ ግን መንግስት "ህገወጦችን" በማገዝ አጥቢያ ቤተክርስቲያናት እንዲሰበሩ፣ መንበረ ጵጵስናዎች እንዲያዙ፣ ምእመናን እንዲዋከቡ እና እንዲገደሉ አድርጓል የሚል ክስ አቅርባለች።
ባለፈው አርብ ቤተክርስቲያኗ ችግሩን ለመፍታት ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ጋር መነጋገሯን እና ጠቅላይ ሚኒስትሩም ላቀረበችው ጥያቄ መልስ እንደሰጣት መግለጿ ይታወሳል።