የአውሮፓ ህብረት “የኤርትራ ወታደሮች በፍጥነት” ይውጡ የሚል የውሳኔ ሀሳብ አሳልፏል
የኢትዮጵያ መንግስት በህብረቱ የውሳኔ ሀሳቡ ቅር መሰኘቱንና እንደማይቀበለው አስታውቋል
የተመድ የሰብአዊ መብቶች ም/ቤት “የኤርትራ ወታደሮች በፍጥነት”ይውጡ የሚለውን የውሳኔ ሃሳብ አጽድቆታል
የአውሮፓ ህብረት በውጭ ጉዳይ ሚኒሰትሮቹ በኩል በኢትዮጵያ ትግራይ ጉዳይ እና የተለያዩ አንገብጋቢ አጀንዳዎች ላይ ላለፉት ቀናት ሲመክር መቆየቱ ይታወቃል፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮቹ ስብሰባ መጠናቀቁን ተከትሎም የህብረቱ የውጭ እና የደኅንነት ጉዳይ ኃላፊ ጆሴፍ ቦሬል አባል ሀገራት በትግራይ ቀውስ ምክንያት በኢትዮጵያ ላይ ማዕቀብ ለመጣል ከግምት እንዲያስገቡ ከሰዓታት በፊት ጠይቀው ነበር፡፡
ቦሬል "ትክክል ናቸው ብለን በምናምንበት ገዳቢ እርምጃዎችን ለመጠቀም ዝግጁ መሆን አለብን" ማለታቸውንም ጭምር የሚታወስ ነው፡፡ይህን ተከትሎም በትግራይ ከሰብዓዊ መብት መከበር ጋር በተያያዘ የአውሮፓ ህብረት የውሳኔ ኃሳብ አሳልፏል፡፡ የውሳኔ ሀሳቡ“የኤርትራ ወታደሮች በፍጥነት እንዲወጡ” የሚል ነው፡፡
የህብረቱ ውሳኔ በ47ኛው የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብቶች ም/ቤት ተቀባይነት አግኝቷል፡፡
ምክር ቤቱ በኢትዮጵያ በትግራይ ክልል ያለው የመብት ጥሰት ጉዳይን በጽኑ የሚያሳስበውንና ግጭቱን አባብሰዋል ያላቸው የኤርትራ ወታደሮች በፍጥነት እንዲወጡ የሚጠይቀውን የውሳኔ ሃሳብ አጽድቋል፡፡
አሜሪካ በበኩሏ በኢትዮጵያ ትግራይ ክልል በንጹሀን ዜጎች ላይ የሚፈጸሙ የበቀል እርምጃዎችን እንደምታወግዝ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባዋ ኔድ ፕራይዝ በኩል አስታውቃለች፡፡
የውሳኔ ኃሳቡ በግጭቱ ሰለባ የሆኑት አካላት ፍትህ እንዲያገኙ እና ወንጀለኞች እንዲጠየቁ የሚያስችል ትልቅ እርምጃ እንደሆነም ነው በጀኔቫ የዩ.ኤስ. ሚሽን በትዊተር ገጹ ላይ ያሰፈረው፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት በበኩሉ የአውሮፓ ህብረት ውሳኔ “ቅር መሰኘቱ” ከሰዓታት በፊት ባወጣው መግለጫ አስታውቀዋል፡፡
ከስብዓዊ የመብት ጥሰት ጋር በተያያዘ በትግራይ ተፈጽመዋል የተባለውን ወንጀል ለማጣራት የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን እና የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ጽሕፈት በጋራ ምርመራ እንዲያከሂዱ መንግስት መስማማቱና ካለፈው ግንቦት ወር አንስቶ እየተካሄደ መሆኑንና ይህም በመጪው ነሃሴ ወር እንደሚጠናቀቅ መግለጫው አስታውሷል፡፡
የውሳኔ ሀሳቡ በአውሮፓ ህብረት በ 47 ኛው የሰብአዊ መብቶች ም/ቤት ላይ ከተሰየመበት ጊዜ አንስቶ ፣ የኢትዮጵያ መንግስት ውሳኔው እንዲነሳ አቤቱታውን ሲያቀርብ መቆየቱ፣ ምክንያቱም ደግሞ ውሳኔው ጊዜው ያልጠበቀና እየተካሄዱ ባለው የጋራ ምርመራዎች ጣልቃ የሚገባ እንዲሁም ታማኝነት የሚያደፈርስ ነው የሚል መሆኑንም መግለጫው አስታውቀዋል፡፡
ምርመራው እስኪጠናቀቅ አስፈላጊውን ጊዜና ቦታ እንዲሰጠው የኢትዮጵያ መንግስት ለምክር ቤቱ እንደተማጸነም ጭምር ነው የተገለጸው፡፡
“ሁሉም ጥረቶቹ አልተሳኩም ፣ከፖለቲካ ጋር ተያያዥነት ያለው ውሳኔ ወቅታዊ ነው ለማለት የሚያስችል የሞራልም ሆነ የሕግ መሠረት የለም፡፡ ምክር ቤቱ በችኮላ ከወሰነው ውሳኔ ይልቅ የተጀመሩ ጥረቶችን በፍጥነት ወደ ስኬታማ መደምደሚያ ለማምጣት ገንቢ ተሳትፎና አስተዋፅዖ ሊኖረው ይችል ነበር፡ በእነዚህ ምክንያቶችም ኢትዮጵያ ይህንን ውሳኔ አትቀበልም ” ሲልም ነው መንግስት በመግለጫው ያስታወቀው፡፡
“በወንጀል ሲሳተፉ የነበሩ ለፍርድ እንደሚቀርቡ እና በሕግ ሙሉ እንደሚቀጡ የታወቀ ይሁን”ም ብሏል፡፡ መንግስት ሀገራዊ እና አለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ግዴታዎችን ለመወጣት በድጋሚ ቃል እንደሚገባ መግለጫው ጠቅሷል፡፡