በትግራይ “የመብራትና የስልክ ግንኙነቶች በፍጥነት” ለማስጀመር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቁርጠኛ መሆናቸውን ተመድ ገለጸ
ዋና ጸሃፊው አንቶንዮ ጉተሬዝ የጠቅላይ ሚኒሰትሩን ምላሽ በበጎ መቀበላቸው ተገልጿል
መሰረታዊ አገልግሎቶቹ ይጀምራሉ ስለሚለው የተመድ መግለጫ በኢትዮጵያ መንግስት በኩል እስካሁን የተሰጠ ይፋዊ መግለጫ የለም
በትግርይ “የመብራትና የስልክ ግንኙነቶችን ጨምሮ አስፈላጊ መሠረታዊ አገልግሎቶች በፍጥነት እንደሚጀምሩ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ቁርጠኛ መሆናቸውን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) ገለጸ፡፡
ጠቅላይ ሚኒሰትሩ ይህንን ያሉት በትግራይ ያለውን የሰብዓዊ ሁኔትን በማስመለከት ከተመድ ዋና ጸሃፊው አንቶንዮ ጉተሬዝ ጋር ከአንድ ቀን በፊት በነበራቸው የስልክ ቆይታ እንደሆነም ነው የዋና ጸሃፊው ቃል የቃል አቀባይ ባወጡት መግለጫ ያስታወቁት፡፡
ጠቅላይ ሚኒሰትሩ የስብዓዊ እርዳታ ሰጪዎች ካለ ምንም ገደብ ወደ ትግራይ የሚገቡበት ሁኔታ መንግስት እንደሚያመቻችም እንዲሁ ቃል መግባታቸው ተመድ ገልጿል፡፡መግለጫው ዋና ጸሃፊው ጉተሬዝ በበኩላቸው የጠቅላይ ሚኒሰትሩ ማረጋገጫ በበጎ መቀበላቸውን ጠቅሷል፡፡
ተመድ እንደዚህ ቢልም ግን በትግራይ ክልል ተቋርጠዋል የሚባለው የመብራትና የስልክ ግንኙነቶች እንዲሁም ሌሎች መሰረታዊ አገልግሎች በፍጥነት ይጀምራሉ ለሚለው በኢትዮጵያ መንግስት በኩል እስካሁን የተሰጠ ይፋዊ መግለጫ የለም፡፡
የኢትዮጵያ መንግሰት በረራዎች በተመለከተ የሰብአዊ እርዳታ የአለም አቀፍ ተቋማት የበረራ ፍቃድ ቢሰጥም፤ ከውጭ ወደ ኢትዮጵያ የሚደረጉ በረራዎች ወደ ትግራይ ከማቅናታቸው በፊት መጀመርያ በአዲስ አበባ ኤርፖርት ሊያርፉ እንደሚገባ ማስታወቁ አይዘነጋም፡፡
የሰብኣዊ እርዳታ ሰጪዎች መንግስት ባዘጋጀቸው መመርያዎች እና መረጃዎች መሰረት ከውጭ ጉዳይ ሚኒሰቴር እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ፈቃድ ማግኘት አንዳለባቸውም ነው መንግስት ያሳሰበው፡፡
ዋና ጸኃፊው አንቶኒዮ ጉተሬዝ የኢትዮጵያ መንግስት የወሰደው የተናጠል ተኩስ አቁም እርምጃ እውቅና እንደሚሰጡም ነው የተገለጸው፡፡
የተወሰደው የተናጠል ተኩስ አቁም እርምጃ “ወደ ትግራይ የሚደረጉ የተመድ ሰብዓዊ እርዳታ በረራዎችና የግብርና ስራዎች እንዲሳለጡ እንዲሁም አስቸኳይ የሰብዓዊ እርዳታ ተደራሽነት ለማመቻቸት የሚያስችል ነው” ብለዋል ጉተሬዝ፡፡
ጉተሬዝ አክለው ሁሉም አካላት ሲቪሎችን የመጠበቅ ግዴታቸውን እንዲወጡ አሳስቧል፡፡
የግጭቱ ተወናዮች በክልሉ ያልተገደበ የሰብዓዊ እርዳታ ተደራሽነት እንዲኖር በማድረግና እንዲሁም ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ሕጎችን በማክበሩ ረገድ ኃላፊነታቸው ሊውጡ ይገባልም ማለታቸውንም ነው የዋና ጸሃፊው ቃል አቀባይ ባወጡት መግለጫ አስታውቋል፡፡