ዓለም አቀፍ ለጋሽ ድርጅቶች በትግራይ የሚያደርጉትን ድጋፍ በፍጥነት ሊያሳድጉ ይገባል- የፀጥታው ም/ቤት
ምክር ቤቱ የኢትዮጵያ መንግሰት ያወጀው የተናጥል ተኩስ አቁም አድንቋል
ለትግራይ ህዝብ ሲባልና ለሰብአዊ ድጋፍ ሁሉም አካል አስቸኳይ የተኩስ አቁም ሊያደርግ ይገባል
ዓለም አቀፍ ለጋሽ ድርጅቶች በትግራይ የሚያደርጉትን ድጋፍ በፍጥነት እንዲያሳድጉ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ጠየቀ።
የተመድ የጸጥታው ምክር ቤት በዛሬው እለት በትግራይ ወቅታዊ ጉዳይ ላይ ውይይት አድርጓል።
በውይይቱም በትግራይ ክል የሚፈጸሙ የሰዓዊ መብት ጥሰቶች በአፋጣኝ ሊቆሙ እንደሚገባ እና ወደፊትም እንዳይፈጸሙ ለዜጎች ጥበቃ ሊደረግ እንደሚገባ አስታውቋል።
በድንበር የለሽ የሀኪሞች ቡድን ላይ የተፈጸመው ግድያ እንዳሳዘነው ያስታወቀው ምክር ቤቱ፤ የሰብአዊ ድጋፍ ሰራተኞች አስፈላጊው ጥበቃ ተደርጎላቸው ያለገደብ ስራቸውን እንዲሰሩ ሊደረግ ይገባል ብሏል።
በክልሉ የሚንቀሳቀሱ ሁሉም የታጠቁ ሀይሎች የሰብአዊ ድጋፍ ሰራተኞችን እና የሲቪሊያንን ደህንነት መጠበቅ እንዳለባቸውም ምክር ቤቱ አሳስቧል።
ከሰሞኑ ዋነኛ ሰብአዊ ድጋፍ መተላፊያ የሆኑ ድልድዮች መውደም በተለይም የተከዜ ድለድይ መፍረሱ አሳሳቢ መሆኑን ያነሳው ምክር ቤቱ፤ ሆኖም ግን መንግስት ሰብአዊ ድጋፎችን ለማጓጓዝ ወደ መቀሌ በረራ መፍቀዱን አድንቆ፤ ወደ ሌሎች አውሮፕላን ማረፊያዎችም በቅርቡ በረራዎችን እንደሚፈቅድ እምነት እንዳለውም ምክር ቤቱ አሳውቋል።
በክልሉ የሰብአዊ ድጋፍ ፈላጊዎች ቁጥር በእጅጉ እያሻቀበ መምጣት እና በተመድ ስር በሚገኙ የሰብአዊ ድጋፍ አቅራቢዎች አማካኝነት አሁን በትግራይ ውስጥ የተከማቸው የእርዳታ መጠን ከአንድ ወር በላይ መቆየት የማይችል መሆኑ በውይይቱ ተነስቷል።
ስለዚህም ዓለም አቀፍ ለጋሽ ድርጅቶች በክልሉ የሚያደርጉትን ድጋፍ በፍጥነት ሊያሳድጉ እንደሚገባም ምክር ቤቱ ጠይቋል።
በክልሉ የስልክ፣ የኤልክትሪክ እና የባንክ አገልግሎቶችን ጨምሮ ሌሎችም መሰረታዊ አገልግሎቶች በፍጥነት ወደ ነበሩበት እንዲመለሱም ጠይቋል።
ምክር ቤቱ በስብሰባው አክሎም የኢትዮጵያ መንግስት ያደረገውን የተኩስ አቁም ያደነቀ ሲሆን፤ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብም የመንግስትን ጥረት ሊያበረታታ ይገባል ብሏል።
በግጭቱ የሚካፈሉ ሌሎች አካላትም በፍጥነት ወደ ተኩስ አቁም ሊመጡ እንደሚገባም ምክር ቤቱ ጥሪ አቅርቧል።
በክል የሚደረጉ የተኩስ አቁሞች በሁሉም የትግራይ ክልል አካባቢዎች ሰብዓዊ ድጋፎችን ለማድረስ ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው ብለዋል።
ለዘላቂ ሰላም ሁሉንም ባለድርሻ አካላት ያካተተ ሀገር አቀፍ ውይይት እና ንግግር ጊዜ ሳይወስድ እንዲጀመር ምክር ቤቱ ጠይቋል።
ኢትዮጵያ ሰኔ 14 ያካሄደችው ምርጫ “በአንዳንድ ቦታዎችና ምርጫ ጣቢያዎች ከታየው እጥረት እና ከፈጠረው ጫና ውጭ ምርጫው ሰላማዊ እና ህጋዊ ሂደቶችን ጠብቆ የተከሄደ ነበር” በሚል የአፍሪካ ህብረት ታዛቢ ቡድን ያቀረበውን ሪፖርት እንደሚቀበልም አስታውቋል።
ምርጫው በኢትዮጵያ ትርጉም ያለው ሁሉንም ባለድርሻ አካላት ያካተተ ወይይት ለማድረግ በር የሚከፍት መሆኑም ምክር ቤቱ አመላክቷል።
በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የኢትዮጵያ ቋሚ መልእክተኛ አምባሳደር ታዬ አጽቀስላሴ፤ ስብሰበዋው የኢትዮጵያ መንግስት ለትግራይ ህዝብ ሲል ትልቅ ፖለቲካዊ ውሳኔ ባሳለፈበት ወቅት መካሄዱን አስታውቀዋል።
መንግሰት ያወጀው የተናጥል ተኩስ አቁም በክልሉ የሚደረጉ የሰብኣዊ ድጋፎችን ለማሳደግ እና ሁሉን አካታች ውይይት ለማድረግ ሰፊ እድል የሚፈጥር ነው ብለዋል።
በመንግስት በኩል እየተሰሩ ያለ ስራዎች ሊበረታቱ እና እውቅና ሊሰጣቸወ ይገባል ያሉት አምባሳደር ታዬ፤ መንግስት በክልሉ የሚደረገውን ሰብአዊ ድጋፍ ለማሰደግ በሚል ነው ተኩስ አቁም ያወጀው ብለዋል።
“ሆኖም ግን የህወሓት ሀይሎች በርከታ ትንኮሳዎችን እየፈጸሙ ነው፤ መንግሰት ለትግራይ ህዝብ ሲል በሆደ ሰፊነት እያለፈ ነው” ሲሉም ተናግረዋል።
መንግስት አሁን ላይ ሰፋ ያለ ሰብአዊ ድጋፍ ስራ እንዲሰራ እድል ሰጥቷል፤ የኢትዮጵያ መንግስት አደጋ ስራ አመራር ኮሚሽን እና 5 የተረአዶ ድርጆቶች በሁሉም የትግራይ ክልሎች ውስጥ ሰብአዊ ድጋፍ ለማድረስ እየሰሩ ነውም ብለዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት በትግራይ ያለውን ቀውስ ለመቅረፍ ከሁሉም ወዳጆቹ ጋር በቅርበት እንደሚሰራም አምባሳደሩ አሳውቀዋል።
መንግስት በሰብዓዊ መብት ጥሰት ተሳተፉ አካላትን ተጠያቂ ለማድረግ እየሰራ መሆኑነ በመጥቀስ፤ በሀገሪቱ ላይ ያለአግባብ የሚደረጉ ጫናዎች ሊቆሙ እንደሚገባ ጠይቀዋል።
የምክር ቤቱ አባላት ኢትዮጵያ እያሳለፈች ያለችውን ፈተና ሊረዱ እንደሚገባ እና የኢትዮጵያ መንግስት ሰላምን ለማምጣት እየወሰደ ላው እርጃ ተገቢውን እውቅና ሊሰጡ እንደሚገባም ጠይቀዋል።
ዓለም አቀፍ ለጋሽ ድርጅቶች በመላው ኢትዮጵያ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ዜጎች የሚያደርጉትን ሰብዓዊ ድጋፍ እንዲያሳድጉም ጠይቀዋል።