የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን ለኢትዮጵያ የ170 ሚሊየን ዩሮ ድጋፍ አደረገ
ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በኢትዮጵያ የሁለት ቀናት ይፋዊ የስራ ጉብኝት በማድረግ ላይ የሚገኙት አዲሷ የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን ፕሬዝዳንት ኡርስላ ቮን ደር ለየንን በፅህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩና የኮሚሽኑ ፕሬዝዳንት የቆየውን የኢትዮጵያና የአውሮፓ ህብረት ግንኙነት ይበልጥ ማጠናከር በሚቻልበት ጉዳይ ላይ መክረዋል፡፡
በዚሁ ወቅት በኢትዮጵያ እና በአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን መካከል የ170 ሚሊየን ዩሮ ድጋፍ ስምምነት ተፈርሟል፡፡
የድጋፍ ስምምነቶቹ በአራት የተለያዩ ዘርፎች የተፈረሙ ሲሆን የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. የፋይናንስ ሚኒስትር አቶአህመድ ሽዴ እና የ አውሮፓ ህብረት ኮሚሽን የዓለም-አቀፍ ትብብር ኮሚሽነር ዩታ ኧርፒላይነን ናቸው የተፈራረሙት
በስምምነቱ መሰረት የአውሮፓ ህብረት ባጠቃላይ ለኢትዮጵያ ከሚያደርገው የ170 ሚሊየን ዩሮ ድጋፍ፣ 100 ሚሊዮን ዩሮው ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገራት ጋር ያላትን የንግድና ኢኮኖሚ ትስስር ለማሳደግ ቁልፍ ለሆኑ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራሞች፣ በተለይም ለትራንስፖርት እና ሎጂስቲክ ዘርፍ፣ የሚውል ነው ተብሏል፡፡
50 ሚሊዮን ዩሮው ደግሞ ለጤናው ዘርፍ ማሻሻያ የሚውል ሲሆን፣ 10 ሚሊዮን ዩሮው ለቀጣዩ ሀገራዊ ምርጫ ስኬታማነት ለምርጫ ቦርድ ማጠናከሪያ፣ ቀሪው 10 ሚሊዮን ዩሮ ደግሞ ለስራ እድል ፈጠራና ኢንቨስትመንት ዘርፍ ድጋፍ የሚውል ነው፡፡
የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽንን በፕሬዝዳንትነት ለመምራት ከተሰየሙ አንድ ሳምንት እንኳን ካልሞላቸው ኡርስላ ቮን ደር ለየን ጋር በነበራቸው ቆይታ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የእንኳን ደስ ያለዎት መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
የአውሮፓ ህብረት፣ የዛሬውን ጨምሮ፣ ለኢትዮጵያ ስለሚያደርገው ዘርፈ ብዙና የማያቋርጥ ድጋፍ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ምስጋናቸውን አቅርበው፣ በተደረሰው ስምምነት መሰረት በህብረቱ ኮሚሽን የተደረገው ድጋፍ ሃገር በቀል ማሻሻያውን በቀጥታ ለማገዝ እንደሚውልም ገልጸዋል፡፡
የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን ፕሬዝዳንት ኡርስላ ቮን ደር ለየን በበኩላቸው “የህዝብን ጥቅም በማስቀደም ጽናትና ራዕይ ካለ ከጎረቤት ሀገራት ጋር ሰላም መመስረት እንደሚቻል በማሳየት ኢትዮጵያ ለመላው አህጉር (ለአፍሪካ) እና ከዚያም ባሻገር ተስፋ የፈነጠቀች ሀገር ናት” ሲሉ ተናግረዋል፡፡ ህብረቱ ለኢትዮጵያ እና ህዝቦቿ በቀጣይነትም ዘላቂ ድጋፍ ለማድረግ ቁርጠኛ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
ከአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ መረጋጋት እና የኢኮኖሚ ትስስር ለመፍጠር የመሪነት ሚና እየተወጣች እንደሆነ የገለጹት ደግሞ በህብረቱ በኩል የድጋፍ ስምምነቱን የፈረሙት የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን የዓለም-አቀፍ ትብብር ኮሚሽነር ዩታ ኧርፒላይነን ናቸው፡፡
ፕሬዝዳንቷ ከጠቅላይ ሚንስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ጋር በመሆን የአንድነት ፓርክንም ጎብኝተዋል።
ከአውሮፓ ውጭ ጉብኝት ሲያደርጉ የመጀመሪያቸው የሆነው የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን ፕሬዝዳንት ኡርስላ ቮን ደር ለየን ከአፍሪካ ህብረት አቻቸው ሙሳ ፋኪ ጋርም ተወያይተዋል፡፡
በውይይቱ ወቅት ባደረጉት ንግግር ሁለቱም ህብረቶች ሰላምና የኢኮኖሚ እድገትን የመሳደግ እና ማዳበር ዓላማን አንግበው የተመሰረቱ መሆናቸውን በማውሳት፣ ለዚህ ስኬታማነትም አንድነት ትልቁ መሳሪያ ነው ብለዋል፡፡
የአውሮፓ ህብረት የጋራ ጥቅምን መሰረት ባደረገ የትብብር መንፈስ ከአፍሪካ ህብረት ጋር ይበልጥ ተቀራርቦ እንደሚሰራም ገልጸዋል፡፡ በፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ የአየር ንብረት ለውጥ፣ ቴክኖሎጊ እና መሰል ዘርፎች በትብብር እንደሚሰሩም ነው የተናገሩት፡፡
የአውሮፓ ህብረት በተለያዩ መስኮች ለአፍሪካ የሚያደርገውን ድጋፍ ያደነቁት የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ፕሬዝዳንት ሙሳ ፋኪም ህብረቱ ከአውሮፓ ህብረት ጋር በትብብር መስራቱን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡
አፍሪካ እና የአውሮፓ ህብረት ጠንካራ ግንኙነት ያላቸው ሲሆን ካጠቃላይ የአፍሪካ የወጪ ንግድ 36 በመቶው ከህብረቱ አባል ሀገራት ጋር የሚፈጸም ነው፡፡ ከአውሮፓ ህብረት የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት 40 በመቶው ወደ አፍሪካ የሚመጣ እንደሆነ የኮሚሽኑ መረጃ ያመለክታል፡፡ ህብረቱ በየአመቱ በአማካይ 22 ቢሊዮን ዩሮ የሚገመት የልማት ድጋፍ ለአፍሪካ እንደሚያደርግም እንዲሁ፡፡
እንደ ሀገር ኢትዮጵያ ደግሞ ከአውሮፓ ህብረት ቀንደኛ አጋሮች መካክል የምትጠቀስ ሀገር ናት፡፡ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ደግሞ ኢትዮጵያ የምታከናውናቸው ሪፎርሞች የሁለቱ አካላት ግንኙነት ይበልጥ እንዲጎለብት ማድረጉ ይታመናል፡፡
ምንጭ፡- የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን