የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን ፕሬዝዳንት አዲስ አበባ ገቡ
አዲሷ የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን ፕሬዝዳንት ኡርስላ ቮን ደር ለየን በኢትዮጵያ የሁለት ቀናት ይፋዊ የስራ ጉብኝት ለማደረግ ዛሬ ህዳር 27 ቀን 2012 ዓ.ም. ጧት ላይ አዲስ አበባ ገብተዋል።
የኮሚሽኑ ፕሬዝዳንት ኡርስላ ቮን ደር ለየን አዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ የኢፌዲሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው እና ሌሎች ከፍተኛ ባለስልጣናት አቀባበል አድርገውላቸዋል።
ፕሬዝዳንት ኡርስላ ቮን ደር ለየን በኢትዮጵያ በሚኖራቸው ቆይታ ከኢፌዲሪ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ እና ሌሎች ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር በኢትዮጵያ እና በአውሮፓ ኮሚሽን መካከል ያለውን ግንኙነት ማጠናከር በሚቻሉባቸው ጉዳዮች ዙሪያ እንደሚወያዩ ይጠበቃል።
ኡርስላ ቮን ደር ለየን በቅርቡ የአውሮፓ ኮሚሽን ፕሬዝዳንት ሆነው ከተመረጡ ወዲህ ከአውሮፓ አገራት ውጭ የመጀመሪያ የሆነውን ጉብኝታቸውን ነው በኢትዮጵያ የሚያደርጉት።
የኢትዮጵያ እና የአውሮፓ ኮሚሽን ኦፊሴላዊ ግንኙነት የተጀመረው በ1967 ዓም ኢትዮጵያ ከአፍሪካ እንዲሁም ከካሪቢያንና ከፓስፈክ አገሮች ጋር በሎሜ በደረሱት የኮቶኖ ስምምነት መሰረት ነው።
የአውሮፓ ህብረት በዚያው ዓመት ጽ/ቤቱን በአዲስ አበባ በመክፈት ግንኙነቱ ተጠናክሮ የቀጠለ ሲሆን፣ ኢትዮጵያም ቤልጄም ብራሰልስ በሚገኘው ኤምባሲዋ በኩል የሁለቱን ግንኙነት አጠናክራ በማስቀጠል ላይ እንደምትገኝ የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር አስታውቋል።
ምንጭ፡- ኢቢሲ