የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ለአዳዲስ ተማሪዎቹ በከተማዋ ቤተሰብ ማዘጋጀት ጀመረ
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ በዚህ ዓመት ዩኒቨርሲቲውን የተቀላቀሉ አዳዲስ ተማሪዎችን ለከተማዋ ወላጆች ሊያስረክብ መሆኑን አስታውቋል፡፡
የዩኒቨርሲቲው የአካዳሚክ ምክትል ፕሬዝዳንት ካሳው ተገኜ (ዶ/ር) ለአማራ ብዙኃን መገናኛ ድርጅት እንደገለጹት በዩኒቨርሲቲው የሚገኙ 5 ሺህ አዳዲስ ተማሪዎችን ‹‹ለወላጆች በመስጠት ነገ ሕዳር 27 ቀን 2012 ዓ.ም የመጀመሪያ ዙር ርክክብ ይደረጋል›› ነው ያሉት፡፡
በጎንደር ከተማ የሃይማኖት ተቋማትን ጨምሮ በተደረገ የቅስቀሳ ሥራ ከተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች የመጡ ተማሪዎችን በጎንደር ቆይታቸው እንደወላጅ ለመያዝ ፈቃደኛ የሆኑ ወላጆች ነገ 1 ሺህ 500 የአደራ ልጆቻቸውን እንደሚረከቡ ነው የገለጹት፡፡
ይህ ርክክብ የመጀመሪያው እንደሆነ የገለጹት ዶክተር ካሳው 5 ሺህ ተማሪዎችን ለወላጆች የመስጠት ሥራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተናግረዋል፡፡
የጎንደር ከተማ ወላጆችም በሚታወቁበት የእንግዳ አቀባበልና የኢትዮጵያዊነት ባሕል ልጆቹን በአደራ መልክ በመውሰድ ለመንከባከብ ፈቃደኝነታቸውን እያሳዩ እንደሆኑ ገልጸዋል፡፡ ነገ ሕዳር 27 ቀን 2012 ዓ.ም በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ከተለያዩ አካባቢዎች የመጡ ተማሪዎች የአደራ ወላጆቻቸውን የሚተዋወቁ ይሆናል፡፡
ይህ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ተግባር ኢትዮጵያውያኝኝ ይበልጥ የሚያስተዋውቅ፣ የሚያቀራርብ እና አንድነትን እና መተሳሰብን የሚያጎለብት ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በዩኒቨርሲቲዎች በተለያየ መልኩ የሚፈጠሩ አላስፈላጊ አለመግባባቶችን እና ግጭቶችን ለመከላከልም ሁነኛ አስተዋጽኦ ያለው በመሆኑ በሌሎችም መሰል ተቋማት ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል፡፡
ምንጭ፡-አብመድ