በ2024 የአውሮፓ ዋንጫ የምድብ ጨዋታዎች እስካሁን ምን ውጤት ተመዘገበ?
አዘጋጇ ሀገር ጀርመን በ6 ነጥብ ምድቧን በመምራትጥሎ ማለፉን የተቀላቀለች የመጀመርያ ሀገር ሆናለች
የጥሎ ማለፍ ጨዋታዎች በሚቀጥለው ሳምንት ቅዳሜ መከናወን ይጀምራሉ
በጀርመን አዘጋጅነት በመካሄድ ላይ የሚገኘው 17ኛው የአውሮፓ ዋንጫ ሰባተኛ ቀኑን ይዟል።
በውድድሩ ጀርመን ፣ ፈረንሳይ ፣ እንግሊዝ እና ስፔን ዋንጫውን ለማንሳት ከፍተኛ ቅድመ ግምት ከተሰጣቸው ሀገራት መካከል ይጠቀሳሉ፡፡
የምድብ ሁለተኛ ጨዋታዋን ትላንት ያደረገችው ጀርመን በጀማል ሙሲያላ እና ኤልካይ ጉንዶጋን ግቦች ሃንጋሪን ሁለት ለዜሮ በመርታት 16ቱን የተቀላቀለች የመጀመሪያዋ ሀገር መሆኗን አረጋግጣለች፡፡
በመክፈቻው ጨዋታ በአዘጋጇ ሀገር 5 ለ1 የተሸነፈችው ስኮትላንድ በበኩሏ ከሲውዘርላንድ ጋር አንድ አቻ በመለያየት በውድድሩ ያላትን ቆይታ አለምልማለች፡፡
እስካሁን 4 ነጥቦችን የሰበሰበችው ሲውዘርላንድ በምድቡ ከጀርመን በመቀጠል በሁለተኛ ደረጃ ላይ ስትገኝ እሁድ ከጀርመን ጋር በሚኖራት ጨዋታ አቻ አልያም ማሸነፍ 16ቱን እንድትቀላቀል ያደርጋታል፡፡
በሁለት ጨዋታዎች አንድ ነጥብ ብቻ ያገኘችው ስኮትላንድ በውድድሩ ደካማ እንቅስቀሴ እያሳየ ከሚገኘው የሀንጋ ብሄራዊ ቡድን ጋር የሚኖራት ጨዋታ ጥሎ ማለፉን ለመቀላቀል ወሳኝ ነው፡፡
ውድድሩ ዛሬም ቀጥሎ ሲደረግ ስሎቫኒያ ከሰርቢያ ከቀኑ 10 ሰአት ፣ ዴንማርክ ከእንግሊዝ ምሽት አንድ ሰአት ፣ ስፔን ከጣሊያን ምሽት 4 ሰአት ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ፡፡
ሰርቢያ እና ዴንማርክ በበኩላቸው በውድድሩ ለመቆየት በዛሬው ጨዋታ የሞት ሽረት ትግል እንደሚያደርጉ ይጠበቃል፡፡ የእንግሊዙ አሰልጣኝ ጋሬዝ ሳውዝጌት ሉክ ሾ ከጉዳት አለማገገሙን ተከትሎ የአሰላለፍ ለውጥ እንደሚያደርጉ አስታውቀዋል፡፡
አሰልጣኙ ከመጀመርያው ጨዋታ በተለየ በሚከተሉት አሰላለፍ ፎደንን በግራ መስመር እንደሚያጫውቱት የገለጹ ሲሆን አርኖልድ ደግሞ በአማካይ ስፍራ ይሰለፋል ብለዋል፡፡
በዋንጫው ከፍተኛ ግምት የተሰጣቸው የስፔን እና የእንግሊዝ ጨዋታዎች ተጠባቂ ሲሆኑ ጣሊያን፣ ስፔን እና እንግሊዝ የመጀመርያ የምድብ ጨዋታዎቻቸውን ማሸነፍ ችለዋል፡፡
የሞት ምድብ በተባለው ምድብ ውስጥ የሚገኙት ስፔን እና ጣሊያን ለምድቡ መሪነት ብርቱ ፉክክር እንደሚያደርጉ ይጠበቃል።
ነገ በሚደረጉ ጨዋታዎች ስሎቫኪያ ከዩክሬን ፣ ፖላንድ ከኦስትሪያ፣ ፈረንሳይ ከኔዘርላንድ ይጫወታሉ፡፡ ፈረንሳይ ኦስትሪያን 1 ለ 0 በሆነ ውጤት በረታችበት የመጀመርያ የምድብ ጨዋታ የአፍንጫ መሰበር ጉዳት ያጋጠመው ፈረንሳዩ አጥቂ ኪሊያን ምባፔ ወደ ልምምድ ቢመለስም በነገው ጨዋታ ላይ መሰለፉ አልተረጋገጠም፡፡