በአውሮፓ ዋንጫ የሞት ምድብ በተባለው ምድብ 2 የተደለደሉ ሀገራት እነማን ናቸው?
2024ቱ የአውሮፓ ዋንጫ የሞት ምድብ 2 የሆነው ጨዋታዎች ዛሬ ምሽጽ ቀጥለው ይካሄዳሉ
በምድብ የምትገኝው የ3 ጊዜ የዋንጫው አሸናፊ ስፔን ተፎካካሪ ልትሆን እንደምትችል ሰፊ ግምት ተሰጥቷታል
የ2024ቱ የአውሮፓ ዋንጫ ትናንት ሲጀመር አስተናጋጇ ሀገር ጀርመን ስኮትላንድን 5ለ1 በማሸነፍ ግስጋሴዋን ጀምራለች።
በዚህ ዋንጫ በቡድን ስብስባቸው እና በልምዳቸው በርካታ ሀገራት የአሸናፊነት ግምቱን ሲያገኙ የሞት ምድብ በተባለው በምድብ 2 የተደለደሉ ስፔን ፣ ጣሊያን ፣ ክሮሽያ እና የአለባኒያ ጨዋታ ሰፊ ትኩረትን አግኝቷል፡፡
ከዚህ ምድብ ውስጥ ወደ 16ቱ የሚገቡ ቡድኖች ዋንጫውን የማሸነፍ አድል ሊኖራቸው እንደሚችልም የስፖርት ተንታኞች እየተናገሩ ነው
ስፔን
በሊዊስ ዲላ ፎንቴ የሚመራው የስፔን ብሔራዊ ቡድን ጠንካራ የቡድን ስብስብ ካላቸው የውድድሩ ተሳታፊዎች መካከል አንዱ ነው።
ቡድኑ በ1984 ፣ 2008 እና በ2012 የአውሮፓ ዋንጫን ለሶስት ጊዜ ማንሳት የቻለ ሲሆን ቡድኑ በ2016 ለሩብ ፍጻሜ ደርሶ በጣሊያን ተሸንፎ ከውድድሩ ውጭ ሆኗል።
በ2022 ሊዊስ ኢንሪኬን በመተካት አሰልጣኝ የሆኑት ሊዊስ ዲላ ፎንቴ የወጣት ቡድኖችን በሚያሰለጥኑበት ወቅት ከበርካታ የብሄራዊ ቡድኑ ተጫዋቾች ጋር ይተዋወቃሉ፣ ይህም የተጫዋቾቹን አቅም ለማወቅ እና ተፎካካሪ ቡድን ለመግንባት እድል የሚሰጣቸው እንደሚሆን ተነግሯል።
በባርሴሎና በመጫወት ላይ የሚገኝው የ16 አመቱ የክንፍ ተጫዋች ላሚን ያማል እና የማችስተር ሲቲው አማካይ ሮድሪጎ ሄርናንዴዝ በብሔራዊ ቡድኑ ከፍተኛ ግልጋሎት እንደሚሰጡ ይጠበቃል።
የስፔን ብሔራዊ ቡድን በምድቡ እና በአጠቃላይ በውድድሩ ብዙ ርቀት ከሚጓዙ ምናልባትም የዋንጫ ተፎካካሪ ከሚሆኑ ቡድኖች መካከል ከምድቡ የቀደሚነት ግምት አግኝቷል።
ክሮሺያ
ለ7ተኛ ግዜ የሚሳተፉት ክሮሺያዎች በውድድሩ ከሩብ ፍጻሜ የተሻገረ ታሪክ የላቸውም፡፡ የአውሮፓ ዋንጫ ርሀብ ያለበት ቡድኑ በዚህኛው አመት የሚገኝበት ምድብ ርሀቡን ለማስታገስ በሚያደርገው ጥረት ፈተና እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡
የብሔራዊ ቡድኑ ቁልፍ ሰው የ38 አመቱ ሉካ ሞድሪች በአለም አቀፍ ውድድሮች ላይ ያለውን ደካማ አፈጻጸም ታሪክ ለመቀየር የመጨረሻ ውድድሩ በሆነው በ2024ቱ የአውሮፓ ዋንጫ ብርቱ ጥረት ሊያደርግ ይችላል ነው የተባለው፡፡
የተከላካይ መስመር ተጫዋቹ የ22 አመቱ ጆስኮ ጋቫርዲለ የክሮሽያ የኋላ ደጀን እንደሚሆኑ ከተተነበዩ ተጫዋቾች መካከል አንዱ ነው።
ቡድኑን ለ7 አመታት የመሩት አሰልጣኝ ዝላቶክ ዳሊክ በ2018 የአለም ዋንጫ ለፍጻሜ ተቃርበው በ3ተኛነት በማጠናቀቅ ያጡትን ዋንጫ በዚህኛው ውድድር ለማካካስ ቃል ገብተዋል።
ክሮሽያ ከምድቧ የማለፍ ሰፊ ግምት ቢሰጣትም 16ቱ ውስጥ እና በግማሽ ፍጻሜ ከአዘጋጇ ጀርመን እና እንግሊዝ የሚገጥማት ፉክክር ቀላል አይሆንም፡፡
ጣሊያን
በዘንድሮው ውድድር ማጣሪያ ጨዋታዎች በእንግሊዝ ሁለት ግዜ ተሸንፋ ከዩክሬን ጋር አቻ ወጥታ በዋንጫው እየተሳተፈች የምትገኝው ጣሊያን በ1968 እና በ2020 የአውሮፓ ዋንጫን ማንሳት ችላለች፡።
በ2022ቱ የአለም ዋንጫ ከተሳትፎ ውጭ የነበረችው ሀገር የአለማችን ምርጥ አማካይ የተሰኝውን ኒኮሎ ባሬላን በቡድን ስብስቧ አካታለች።
ኢንተርሚላን በ2022 /23 በሻምፒውንስ ሊጉ ፍጻሜ እንዲደርስ እና በ2023/24 የሴሪአው አሸናፊ እንዲሆን ትልቁን ድርሻ የተወጣው ባሬላ የብሔራዊ ቡድኑ ስብስብ አባል ነው፡።
በ2022ቱ የአለም ዋንጫ ያልተሳተፈው በ2024ቱ የአውሮፓ ዋንጫ ማጣርያ ደካማ አቋም ያሳየው የጣሊያን ብሔራዊ ቡድን በጫና ውስጥ የሚጫወት ቢሆንም በውድድሩ የተሸለ አፈጻጸምን ለማስመዝገብ ብርቱ ተፎካካሪ ከሚሆኑ ቡድኖች መካከል አንዱ ነው፡፡
አልባኒያ
በማጣርያ የምድብ ጨዋታዎች ከቼክ ሪፐብሊክ እና ፖላንድ የተሻለ ነጥብ በመያዝ ከምድባቸው ቀዳሚ ሆነው ያለፉት አልባኒያዊያን በ2016 ከነበራቸው ተሳትፎ ቀጥሎ በአውሮፓ ዋንጫ ሲወዳደሩ ይህ ለሁለተኛ ጊዜያቸው ነው፡፡
በ21 ጨዋታዎች 5 ጎሎችን ያስቆጠረው የቼልሲውን አርማንዶ ብሮጃ በስብስቧ ያካተተችው አልባኒያ በ2023 ባደረገቻቸው 13 ጨዋታዎች 7ቱን ማሸነፍ ችላለች ፡፡
የመጨረሻ ሁለት የአቋም መለኪያ ጨዋታወችን 3ለ0 እና 3ለ1 ያሸነፈው ብሔራዊ ቡድኑ ጥሎ ማለፉን ለመቀላቀል ሶስተኛ ደረጃን ይዞ ማጠናቀቅ በቂው ነው።
በውድድሩ አነስተኛ የተሳትፎ ታሪክ ያለው ቡድኑ ምንም እንኳን አነስተኛ ግምት ቢያገኝም በማጣሪያ እና በአቋም መለኪያ ጨዋታዎች ያሳየው ብቃት አይገመቴ ድልን ሊያስመዘግብ እንደሚችል ተንታኞች ተንብየዋል።