በአውሮፓ ዋንጫ የሚሳተፉ ቡድኖችና ተጫዋቾች ምን ያህል ገንዘብ ያገኛሉ?
የፊታችን አርብ በጀርመን በሚጀመረው የ2024 የአውሮፓ ዋንጫ 357 ሚሊየን ዶላር ለሽልማት ተዘጋጅቷል
በአህጉራዊው ውድድር አሸናፊ የሚሆነው ቡድን 30 ሚሊየን ዶላር ያገኛል ተብሏል
በአራት አመት አንዴ የሚካሄደውና ከአለም ዋንጫ ቀጥሎ በርካቶች በጉጉት የሚጠብቁት የአውሮፓ ዋንጫ አርብ በጀርመን ይጀመራል።
በዚህ 24 ብሄራዊ ቡድኖች በሚሳተፉበት አህጉራዊ ውድድር ለሽልማት 357 ሚሊየን ዶላር ተዘጋጅቷል።
ብሄራዊ ቡድኖቹ በውድድሩ በመሳተፋቸው ብቻ የሚያገኙት ገንዘብ አለ፤ ከምድብ እስከ ፍጻሜ ድረስ በሚያስመዘግቡት ውጤትም የሚከፈላቸውን የገንዘብ መጠን ይፋ ተደርጓል።
ተጫዋቾቹም ከየሀገራቱ ፌደሬሽኖች ደመወዝ የማያገኙ ቢሆንም ከክለቦችና ከፌደሬሽኖች ጋር በሚደረስ ስምምነት መሰረት እንደሚያስመዘግቡት ውጤት ገንዘብ ያገኛሉ ተብሏል።
በልምምድ፣ በጀርመን በሚያሳልፉት ቀናት ቆይታና በሚያስመዘግቡት ውጤት መሰረት ጉርሻ እንደሚያገኙ የስፔኑ ማርካ ጋዜጣ አስነብቧል።
ለአብነትም የጀርመን ብሄራዊ ቡድን የ2024ቱን የአውሮፓ ዋንጫ ካነሳ ሁሉም የቡድኑ ተጫዋቾች 400 ሺህ ዩሮ ወደ ኪሳቸው ይገባል ነው የተባለው።
በ2024ቱ የአውሮፓ ዋንጫ ብሄራዊ ቡድኖች ምን ያህል ገንዘብ ያገኛሉ?
ተሳታፊ ቡድኖች (24) - 9.96 ሚሊየን ዶላር
የጨዋታ ጉርሻ (ቦነስ) - ለአሸናፊ 1.07 ሚሊየን ዶላር ፤ አቻ 530 ሺህ ዶላር
ጥሎ ማለፉን ለሚቀላቀሉ (16) – 1.62 ሚሊየን ዶላር
ሩብ ፍጻሜ ለሚቀላቀሉ (8) - 2.69 ሚሊየን ዶላር
ግማሽ ፍጻሜ ለሚደርሱ (4) – 4.3 ሚሊየን ዶላር
በፍጻሜው ተሸናፊ - 5.4 ሚሊየን ዶላር
ሻምፒዮን - 8.6 ሚሊየን ዶላር
በ2024 የአውሮፓ ዋንጫ ሶስቱንም የምድብ ጨዋታዎች አሸንፎ ሻምፒዮን የሚሆነው ቡድን ከፍተኛ ሊያገኘው የሚችለው ገንዘብ 30.43 ሚሊየን ዶላር ነው።
ተጠባቂው የአውሮፓ ዋንጫ አርብ ጀርመን ከስፖትላንድ በአሊያንዝ አሬና ስታዲየም በሚያደርጉት ጨዋታ ይጀመራል። ፍጻሜውም ሃምሌ 14 2024 ከ74 ሺህ በላይ ተመልካቾችን ማስተናገድ በሚችለው የበርሊን ኦሎምፒክ ስታዲየም ይደረጋል።