የአውሮፓ ሀገራት ከ1 ነጥብ 2 ሚሊዮን በላይ የሰራተኞች እጥረት እንደገጠማቸው ገለጹ
የህክምና ዶክተሮች፣ ነርሶች እና አዋላጅ ሙያዎች በአውሮፓ እጥረት አጋጥሟል ተብሏል
ኖርዌይ፣ ዴንማርክ፣ ሆላንድ እና ጀርመን የሰራተኛ ዕጥረቱ የተባባሰባቸው ሀገራት ናቸው
የአውሮፓ ሀገራት ከ1 ነጥብ 2 ሚሊዮን በላይ የሰራተኞች እጥረት እንደገጠማቸው ገለጹ።
የዓለማችን ሀብታሙ የሚባለው አህጉር አውሮፓ በሰራተኞች ዕጥረት እየተፈተነ ነው ተብሏል።
የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን ባወጣው ጥናት መሰረት በአውሮፓ ሀገራት ያለው የሰራተኞች በተለይም የህክምና ባለሙያዎች ዕጥረት እየተባባሰ ነው ብሏል።
በተለይም ኖርዌይ፣ ዴንማርክ፣ ሆላንድ፣ ጀርመን እና ፊንላንድ የጤና ባለሙያዎች ዕጥረቱ ከፍተኛ ነው ተብሏል።
በህብረቱ አባል ሀገራት የሰራተኞች ዕጥረት እንዲያጋጥም ያደረገው ምክንያት እድሜያቸው እየጨመሩ ያሉ ዜጎች ቁጥር ማሻቀብ፣ ወጣት አውሮፓዊያን በተለይም በጤና ሙያ ላይ የመማር ፍላጎት ማጣት እና ራሳቸው የጤና ባለሙያዎች በቶሎ ጡረታ የመውጣት ፍላጎታቸው በመጨመሩ እንደሆነ ዩሮ ኒውስ ዘግቧል።
የዓለም ጤና ድርጅት በበኩሉ በአውሮፓ ያለው የጤና ባለሙያዎች ዕጥረት በዚሁ ከቀጠለ በ2030 ወደ 4 ሚሊዮን ከፍ ሊል እንደሚችል አስጠንቅቋል።
የጤና ባለሙያዎች እጥረቱ በመላው አውሮፓ ያጋጠመ መሆኑን ተከትሎ ሀገራቱ ከዚህ ችግር የሚወጡበት ወጥ ፖሊሲ እንዲዘጋጅም ጥሪ ቀርቧል።
ሀገራት የገጠማቸውን የሰራተኞች ዕጥረት ለመፍታት ሰው ሰራሽ አስተውሎቶችን፣ ሮቦቶችን እና ሌሎች ቴክኖሎጂዎችን እየተጠቀሙ ቢሆንም የሰው ሀይል የግድ ያስፈልጋል ተብሏል።
የሰለጠኑ ስደተኛ ሰራተኞችን ከተለያዩ ሀገራት መቀበል በዋና አማራጭነት የተወሰደ ሲሆን የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን ይህን የሚያመቻች አሰራር እንዲዘረጋ ተጠይቋል።