በዩክሬን ጦርነት ምክንያት ገበያ የደራላቸው የአውሮፓ ኩባንያዎች እነማን ናቸው?
አራት የአውሮፓ የጦር መሳሪያ አምራች ኩባንያዎች የዩክሬን ጦርነት በረከት ይዞላቸው መጥቷል
የብሪታንያው ቢኤኢ ኩባንያ በስድስት ወራት ውስጥ የ70 ቢሊዮን ዶላር ግዢ ትዕዛዝ ደርሶታል
በዩክሬን ጦርነት ምክንያት ገበያ የደራላቸው የአውሮፓ ኩባንያዎች እነማን ናቸው?
ለአንድ ሳምንት ልዩ ዘመቻ በሚል የተጀመረው የሩሲያ ዩክሬን ጦርነት ሶስተኛ ዓመቱ ላይ ይገኛል፡፡
ይህ ጦርነት ካደረሰው የንጹሃን ሞት፣ መሰደድ እና ንብረት ውድመት ባለፈ ለጦር መሳሪያ አምራች ኩባንያዎች ጥሩ የገበያ እድል ፈጥሯል ተብሏል፡፡
ዩሮ ኒውስ እንደዘገበው ከሆነ አራት የአውሮፓ የጦር መሳሪያ አምራች ኩባንያዎች የዩክሬን ጦርነት ገበያቸውን እንዳደራላቸው ተገልጿል፡፡
እንደዘገባው ከሆነ የጀርመን ሬንሜታል፣ የብሪታንያው ቢኤኢ፣ የፈረንሳዩ ቴልስ እንዲሁም የስዊድኑ ሳብ የጦር መሳሪያ አምራች ኩባንያዎች ገበያ ከደራላቸው ተቋማት መካከል ዋነኞቹ ናቸው፡፡
ከዩክሬን ጀርባ ያሉ የዓለማችን ሀገራት ኪቭን ለመርዳት ሲሉ ያላቸውን የጦር መሳሪያ በመለገሳቸው ምክንያት አዲስ እና ዘመን አፈራሽ የጦር መሳሪያዎችን ለመግዛት ለኩባንያዎቹ ጥያቄ አቅርበዋል፡፡
ለአብነትም የፈረንሳዩ ቴልስ ኩባንያ በተያዘው የ2024 ዓመት ውስጥ ግማሽ ዓመት 47 ቢሊዮን ዩሮ ግዢ ጥያቄ ቀርቦለታል፡፡
እንዲሁም የጀርመኑ ሬንሜታል ኩባንያ እስከ 2028 ድረስ ሰርቶ እንዲያስረክብ ከተለያዩ ሀገራት ጋር ስምምነት ፈጽሟል፡፡
እንዲሁም የብሪታንያው ቢኤኢ ኩባንያ ደግሞ እስከ ሰኔ 30 ባሉት ጊዜ ውስጥ ብቻ 70 ቢሊዮን ዶላር ዋጋ ያላቸው የጦር መሳሪያ ግዢ ስምምነት መፈራረሙ ተገልጿል፡፡
የጦር መርከቦችን በመስራት የሚታወቀው የስዊድኑ ሳብ ኩባንያ በበኩሉ የግዢ ትዕዛዛት ጎርፎለታል የተባለ ሲሆን የሽያጭ ገቢው በ25 በመቶ እንደጨመረለት በዘገባው ለይ ተጠቅሷል፡፡
ከአውሮፓ በተጨማሪ የአሜሪካው ሎክሄድ ማርቲን፣ ኖርዝቶፕ ግሩማን፣ ጀነራል ዳይናሚክስ እና ሌሎችም መሰል ኩባንያዎች ከዩክሬን ጦርነት አትራፊ ኩባንያዎች መካከል ዋነኞቹ ናቸው፡፡