ጀርመን በቀጣዮቹ 15 ዓመታት በየዓመቱ 288 ሺህ ሰራተኞች ያስፈልጓታል ተባለ
ሀገሪቱ የገጠማትን ሰራተኞች እጥረት ለመፍታት በሚል ከአንድ ዓመት በፊት አዲስ የስደተኞች ፖሊሲ ማዘጋጀቷ ይታወሳል
ስደተኞች ጀርመን ለገጠማት የሰራተኞች ዕጥረት ዋነኛው መፍትሄ ሊሆን እንደሚችል ተገልጿል
ጀርመን በቀጣዮቹ 15 ዓመታት በየዓመቱ 288 ሺህ ሰራተኞች ያስፈልጓታል ተባለ፡፡
በአውሮፓ ቁጥር አንድ ሀብታም ሀገር በሆነችው ጀርመን የሰለጠነ ሰራተኞች እጥረት ማጋጠሙ ይታወሳል፡፡
ይህን ተከትሎ ሀገሪቱ የገጠማትን ሰራተኞች ዕጥረት ለመፍታት የስደተኞች ፖሊሲዋን ከአንድ ዓመት በፊት አሻሽላለች፡፡
የጀርመን ድምጽ ሬዲያ ወይም ዶቼቪሌ የበርቴልስማን ፋውንዴሽን ጥናትን ዋቢ አድርጎ እንደዘገበው ከሆነ ሀገሪቱ እስከ 2040 ድረስ በየዓመቱ 228 ሺህ ሰራተኞች ያስፈልጓታል፡፡
ሀገሪቱ አሁን ላይ መስራት የሚችሉት ዜጎቿ ቁጥር 46 ሚሊዮን ሲሆን በ2040 ይህ ቁጥር ወደ 42 ሚሊዮን ዝቅ ይላልም ተብሏል፡፡
እንዲሁም ከሀገሪቱ ጠቅላላ ህዝብ መካከል መስራት የሚችሉት ቁጥር በ2060 ወደ 35 ሚሊዮን ዝቅ እንደሚልም ተገምቷል፡፡
ይህ የሚሆነው ደግሞ በየዓመቱ የሚወለዱ ህጻናት ቁጥር እየቀነሰ የሚሄድ በመሆኑ እንደሆነም በዘገባው ላይ ተጠቅሷል፡፡
ጀርመን ከ500 ሺህ በላይ የሰራተኞች እጥረት እንዳለባት አስታወቀች
ጀርመን የገጠማትን የሰራተኞች እጥረት ለመፍታት ከአንድ ዓመት በፊት ባሻሻለችው ህግ ላይ የመኖሩያ ፈቃድ፣ የስራ ፈቃድ እና የዜግነት አሰጣጥን ሁኔታ የሚያቀሉ አሰራሮችን በመተግበር ላይ ትገኛለች፡፡
ይሁንና የሀገሪቱ የሰራተኞች እጥረት አሁንም ችግር ላይ ነው የተባለ ሲሆን በተለይም የጤና፣ ግንባታ እና ተያያዥ ስራዎች እጥረቱ ከፍተኛ ነው ተብሏል፡፡