ፌስቡክ እና ኢንስታግራም በሶስት ወራት ውስጥ 39 ቢሊዮን ዶላር ገቢ አገኙ
ኩባንያዎቹ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ብዙ ገቢ እንዲያገኙ አስችሏቸዋል ተብሏል
ሜታ ኩባንያ በቀጣይ 40 ቢሊዮን ዶላር በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ላይ ኢንቨስት አደርጋለሁ ብሏል
ፌስቡክ እና ኢንስታግራም በሶስት ወራት ውስጥ 39 ቢሊዮን ዶላር ገቢ አገኙ።
የሜታ ኩባንያ ንብረቶች የሆኑት ፌስቡክ እና ኢንስታግራም ባለፉት ሶስት ወራት ከፍተኛ ገቢ ማግኘታቸውን አስታውቀዋል።
ኢንስታግራም እና ፌስቡክ ባለፉት ሶስት ወራት ውስጥ 39 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘታቸውን አስታውቀዋል።
ሁለቱ ኩባንያዎች ያገኙት ገቢ ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ13 ቢሊዮን ዶላር ወይም የ20 በመቶ ብልጫ አለው ተብሏል።
ኩባንያዎቹ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ መጠቀማቸው ለገቢያቸው መጨመር ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳበረከተ ተገልጿል።
በዓለማችን ካሉ የማህበራዊ ትስስር ገጾች መካከል ተጽዕኖ ፈጣሪ የሆኑት ፌስቡክ እና ኢንስታግራም በሜታ ኩባንያ ስር ካሉ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች መካከል ዋነኞቹ ናቸው።
የድርጅቱ መስራች እና ባለቤት ማርክ ዙከርበርግ እንዳስታወቀው ተወዳዳሪ ለመሆን እና ተጨማሪ ገቢ ለማግኘት እንዲረዳቸው በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ላይ 40 ቢሊዮን ዶላር ወጪ እንደሚያደርጉ አስታውቋል።
መሰረታቸውን አሜሪካ ያደረጉት ሜታ፣ ጎግል እና ማይክሮሶፍት ኩባንያዎች የተሻሻለ የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ መተግበሪያ ለመስራት ፉክክር ላይ ናቸው።
70 ሺህ ሰራተኞች ያሉት ሜታ ኩባንያ በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ አማካኝነት ሰራተኖችን እየቀነሰ ይገኛል።
ድርጅቱ በፈረንጆቹ 2022 ላይ በመላው ዓለም ላይ 80 ሺህ ሰራተኞች ነበሩት።