ኢንስታግራም የተለያዩ ምርትና አገልግሎቶችን ለሚያስተዋውቁ ሰዎችም የገቢ ምንጭ ሆኗል
የሜታ እህት ኩባንያ የሆነው ኢንስታግራም የታዋቂ ሰዎች መንደር ብቻ ሳይሆን ገንዘብ የሚሰራበት የማህበራዊ ትስስር ገጽ ነው።
አዳዲስ የቢዝነስ ሃሳቦችን ለማስተዋወቅና ተደራሽነትን ለማስፋትም 2 ነጥብ 35 ቢሊየን ተጠቃሚ ያለው ኢንስታግራም ተመራጭ መሆኑ ይነገራል።
ኢንስታግራም በ2020 የጀመረውና የቲክቶክ አምሳያ የሆነው የአጫጭር ቪዲዮ (ሪልስ) ማጋሪያውም በአጭር ጊዜ በርካታ ተጠቃሚዎች አፍርቷል።
የኢንስታግራም ተጠቃሚዎች በቀን 17 ነጥብ 6 ሚሊየን ስአት እነዚህን በቪዲዮ ማጋሪያ (ሪልስ) ላይ የሚጫኑ ከ90 ሰከንድ የማይበልጥ ርዝማኔ ያላቸው ቪዲዮዎች በመመልከት ያሳልፋሉ።
ቪዲዮቹን ማጋራት ራስን ወይም የቢዝነስ ድርጅትን ከማስተዋወቅ በዘለለ ገቢ ማስገኘትም ጀምሯል።
እናም ከኣኢንስታግራም አጫጭር ቪዲዮዎች ገንዘብ መስራት የሚቻልበትን መንገድ እንጠቁማችሁ፦
1. የተከታይ ብዛትን ማሳደግ
ኢንስታግራም የቪዲዮ ማጋሪያውን ሲያስተዋውቅ ለይዘት ፈጣሪ ባለሙያዎች 1 ቢሊየን ዶላር ለመክፈል ማሰቡን ይፋ አድርጎ ነበር። ይህን ገንዘብ ለመጠቀምና ከቪዲዮዎቹ ገንዘብ ለማግኘት ግን ያስቀመጣቸው ቅድመ ሁኔታዎች አሉ።
የመጀመሪያው የተጠቃሚው የኢንስታግራም ተከታዮች ቁጥር ከ1 ሚሊየን በታች መሆን አለበት የሚለው ነው። የቢዝነስ ወይም የይዘት ፈጣሪ (ክሬተር) አካውንት መክፈትም የግድ ይላል።
2. ክፍያ ለመጀመር ቪዲዮዎቹ ምን ያህል ተመልካች ያስፈልጋቸዋል?
ኢንስታግራም ላይ የጫነው አጭር ቪዲዮ በ30 ቀናት 1 ሺህ ተመልካች ሲያገኝ የኢንስታግራም ሪልስ ቦነስ ተጠቃሚ መሆን ይችላል። በየጊዜው ቪዲዮዎችን ሲጭንም የቦነስ አማራጩን ማስገባት የተሻለ ተጠቃሚ ያደርገዋል። ይሁን እንጂ ከክፍያ የሚሰሩና የሚተዋወቁ ቪዲዮዎች በዚህ አማራጭ ተጠቃሚ አይሆኑም።
3. በክፍያ ተደራሽነትን ማስፋት
ኢንስታግራም ለምንጭናቸው ቪዲዮዎች ለመክፈል የተመልካቾችን ቁጥር ብቻ አይደለም የሚመለከተው፤ ተምልካቾቹ ያላቸው ተሳትፎንም ያያል። ጀማሪዎችም በዚህ ሲፈተኑ ይታያል። ለዚህም መፍትሄ ተብሎ የቀረበው የላይክ መጠንን የሚያሳድጉ “ኦተንቲክ ላይክስ” መግዛት ነው። በሽያጭ የሚቀርበው አገልግሎት የቪዲዮ ተደራሽነትን ከማስፋት ባለፈ ተአማኝነትን ከፍ ለማድረግም እንደሚያግዝ ይታመናል።
4. ምን ያህል ገንዘብ ይገኛል?
ኢንስታግራም ከሪልስ የሚገኘው ገንዘብ ላይ ገደብ አላስቀመጠም፤ የምናገኘው ገቢ የሚወሰነው የሰራነው ቪዲዮ በሚያገኘው ተመልካች ቁጥር ብቻ ነው። የሰራነውን ገንዘብ ለማውጣት ግን በጥቂቱ 100 ዶላር መሙላት አለበት።
5. የብራንድ ስፖንሰርሺፕ እና ትብብር
ኢንስታግራም ምርትና አገልግሎትን ለማስተዋወቅ ሁነኛ የማህበራዊ ትስስር ገጽ መሆኑ ይነገራል። ዝናቸው ከፍ ያለ ኩባንያዎችም በርካታ ተከታይ ያላቸውንና በፈጠራ ችሎታቸው የተመሰከረላቸውን የኢንስታግራም ተጠቃሚዎች የብራንድ አምባሳደር አድርገው ያሰራሉ። በዚህም ከፍተኛ ገቢ የሚያገኙ ባለተሰጥኦዎች ቁጥር እየጨመረ መጥቷል።
6. በኮሚሽን መስራት
ኢንስታግራም ላይ በስፋት እንዲተዋወቁ የሚፈልጉ ኩባንያዎች የተለያዩ ድረገጽ እና ማህበራዊ ትስስር ገጾች ማስፈንጠሪያዎችን በቪዲዮዎቻችን ላይ በማካተት ገንዘብ ማግኘት ይቻላል። እነዚህን “አፊሌት ሊንኮች” ከሚለቁ ተቋማት በመውሰድና በኮሚሽን ገንዘብ ማግኘት እንደሚቻል ኢንስታግራም ገልጿል።
7. ምርቶችን መሸጥ
ኢንስታግራም የቢዝነ ስራዎችን ለማቀላጠፍ ተመራጭ ከሆኑ ማህበራዊ ትስስር ገጾች ከግንባር ቀደሞቹ ውስጥ ይጠቀሳል። እናም ምርትና አገልግሎትን በቪዲዮዎች ማስተዋወቅ ከቪዲዮዎቹ ከሚገኘው ገቢ ባሻገር ምርትን ለገበያ ለማቅረብ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው። በኢንስታግራም ላይ የኦንላይን ሱቅ በመክፈትም በቀላሉ ምርትን መሸጥ ይቻላል።
8. የአዳዲስ ምርቶች ግምገማ
አዳዲስ ምርትና አገልግሎትን ኩባንያው በሚያሰራው ማስታወቂያ የመቀበል የሰው ልጆች ልማድ እየተለወጠ ይገኛል። ከኩባንያዎቹ ይልቅ ሌሎች ሰዎች የሚሰጡት ምስክርነትም ይበልጥ ተአማኒ እየሆነ ነው። እናም በኢንስታግራም የአዳዲስ ምርቶች ግምገማ (ሪቪው) ማድረግ እየተለመደ መጥቷል። ሃቀኛ የምርትና አገልግሎት ግምገማ ማድረግ በርካታ ተመልካች ከማስገኘቱ ባሻገር ከቪዲዮዎች የምናገኘውን ገቢ ያሳድጋል።
9. የኢንስታግራም መተግበሪያዎችን መስራት
የተለያዩ መተገበሪያዎች (አፕሊኬሽን) መስራት ለሚችሉ የፈጠራ ባለሙያዎች ኢንስታግራም ገንዘብ ይከፍላል። ለኢንስታግራም የሚመቹ የፎቶ ፊልተሮችን ጨምሮ የተለያዩ መተግበሪያዎችን ሰርቶ በመሸጥ በርካቶች ተለውጠውበታል።
ኢንስታግራም አጫጭር ቪዲዮዎችን በመስራት ብቻ ሳይሆን በሌሎች አማራጮችም ገንዘብ መስራት ያስችላል። ዋናው ፈጠራ የታከለበትና ተደራሲን ያማከለ አዲስ ይዘት መቅረብና ተደራሽነቱን ለማስፋት የመጣሩ ጉዳይ ነው።