ከፍጥነት በላይ ያሽከረከረው ፊንላንዳዊ ሰባት ሚሊዮን ብር ተቀጣ
ፊንላንድ ከፍጥነት በላይ የሚያሽከረክሩ ሰዎችን በገቢያቸው መጠን እንዲቀጡ የሚያዝ ህግ አላት
የግለሰቡ የመንጃ ፈቃድም ለ10 ዓመት መታገዱ ተገልጿል
ከፍጥነት በላይ ያሽከረከረው ፊንላንዳዊ ሰባት ሚሊዮን ብር ተቀጣ፡፡
በአውሮፓዊቷ ፊንላንድ አላንድ ደሴት ነዋሪ የሆኑት ባለጸጋው አንድሬስ ዊኮልፍ ከፍጥነት በላይ ሲያሽከረክር ተገኝቶ በታሪክ ትልቁን የትራፊክ ደንብ ጥሰት ቅጣት ተጥሎበታል፡፡
ግለሰቡ በሰዓት እስከ 50 ኪሎ ሜትር ፍጥነት በሚነዳበት መንገድ ላይ በሰጫት 82 ኪሎ ሜትር ፍጥነት በመንዳቱ የ129 ሺህ ዶላር ወይም ሰባት ሚሊዮን ብር ተቀጥቷል ሲል ዶቸቪሌ ዘግቧል፡፡
እንደዘገባው ከሆነ ፊንላንድ የትራፊክ ደንብ የሚጥሱ ሰዎችን በገቢያቸው መጠን መቅጣት የሚያስችላት ህግ ያላት ሲሆን ይህም ባለጸጋ ከፍተኛ የገንዘብ ቅጣት መቀጣቱ ተገልጿል፡፡
ይህ ግለሰብ ከዚህ በፊት በተመሳሳይ በፈረንጆቹ 2018 ላይ ከተቀመጠለት ፍጥነት በላይ ሲያሽከረክር ተይዞ የ68 ሺህ ዶላር ተቀጥቶ በወቅቱ በአውሮፓ መነጋገሪያ ሆነው ነበር ተብሏል፡፡
ለሁለተኛ ጊዜ ከፍጥነት በላይ በማሽከርከር የተያዙት አዛውንቱ ባለጸጋ አሽከርካሪ በአምስት ዓመታት ውስጥ 10 ሚሊዮን ብር ገደማ ለፊንላንድ መንግስት በቅጣት መልኩ ከፍለዋል፡፡
እኝህ ከፍጥነት ወሰን በላይ በማሽከርከር የተከሰሱት ባለጸጋ የመንጃ ፈቃዳቸው ለ10 ዓመት የታገዱ ሲሆን ውሳኔውን በጸጋ መቀበላቸውን ጠቅሰዋል፡፡
የሪልኢስቴት ቱሪዝም እና ሎጅስቲክስ ኩባንያዎች ባለቤት የሆኑት ፊንላንዳዊው ዊኮልፍ " ፍጥነቴን የቀነስኩ መስሎኝ ነበር፣ በሰራሁት ነገር አፍሬያለሁ፣ የከፈልኩትን ገንዘብ መንግስት ለጤና ማሻሻያ ስራዎች እንደሚያውለው ተስፋ አደርጋለሁ" ብለዋል፡፡
አላንድ ዊክሎፍ በስዊድን አጎራባች በሆነችው የፊንላንድ ራስ ገዝ ወደብ ከተማ ነዋሪ ሲሆኑ በከተማዋ ቁጥር አንድ ባለጸጋ ግለሰብም ናቸው፡፡