ፕሬዝዳንት ኤርዶጋን ቱርክ የፊንላንድን የኔቶ አባልነት ጥያቄ እንደምታጸድቅ ገለጹ
ቱርክ፤ የስዊድንን የኔቶ አባልነት ጥያቄን በይደር እንደምታቆየው አስታውቃለች
የቱርክ ፓርላማ የፊንላንድን ጥያቄ ግንቦት 14 ከሚካሄደው የሀገሪቱ ምርጫ በፊት እንደሚያጸድቅ ይጠበቃል
የዩክሬን እጣ ፈንታ እንዳይገጥማቸው የሰጉት ስዊድን እና ፊንላንድ ባለፈው አመት ኔቶን ለመቀላቀል ጥያቄ ማቅረባቸው አይዘነጋም።
- ቱርክ፤ ስዊድን እና ፊንላንድ የአንካራን የጸጥታ ችግር ለመፍታት እርምጃ መውሰዳቸውን ገለጸች
- የቱርክ ፕሬዝዳንት፤ ፊንላንድ ያለ ስዊድን ኔቶን ልትቀላቀል እንደምትችል ፍንጭ ሰጡ
ይሁን እንጅ ሁለቱም ሀገራት በአንካራ እና በምዕራባውያን አሸባሪ ተብለው የሚፈረጁትን የኩርዲስታን ሰራተኞች ፓርቲ አባላትን ያግዛሉ በሚል በቱርክ በኩል ከፍተኛ ተቃውሞ ገጥሞዋቸው ወደ ጥምረቱ ሳይቀላቀሉ መቆየታቸው የሚታወቅ ነው፡፡
ላለፉት በርካታ ጊዜያት ስዊድን እና ፊንላንድን ወደ ኔቶ የመቀላቀል ጥያቄን ስትቃወም የቆየችው ቱርክ አሁን ላይ ሀገራቱ በተለይም ፊንላንድ ወደ ጥምረቱ እንድትቀላቀል ልትፈቅድ እንደምትችል ገልጻለች፡፡
የቱርክ ፕሬዝዳንት የሀገሪቱ ፓርላማ የፊንላንድን የኔቶ አባልነት ጥያቄ እንደሚያጸድቅ አስታውቀዋል፡፡
ኤርዶጋን ከፊንላንድ አቻቸው ሳኡሊ ኒኒስቶ ጋር በአንካራ ያደረጉትን ውይይት ተከትሎ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ሄልሲንኪ የቱርክን ፍቃድ እንዳገኘች ገልጸዋል፡፡
ፊንላንድ የቱርክን ይሁንታ ያገኘቸው አንካራ በአሸባሪነት የምትመለከቷቸውን ነገሮች ለመመከት እና የመከላከያ ምርቶችን ለማስለቀቅ የገባቸውን ቃል ለመፈጸም ተጨባጭ እርምጃዎችን በመውሰዷ ነውም ብለዋል፡፡
“የፊንላንድን ወደ ኔቶ የመቀላቀል ሂደት ለማጸደቅ ወስነናል”ም ነው ያሉት ፕሬዝዳንቱ፡፡ ከግንቦት 14 ምርጫ በፊት ፓርላማው ጥያቄውን እንደሚያጸድቀው ያላቸውን ተስፋ በመግለጽ።
ኒኒስቶ በበኩላቸው ውሳኔውን ከሩሲያ ጋር ረጅም ድንበር ለምትጋራው ፊንላንድ ጠቃሚ በመሆኑ በደስታ እንደሚቀበሉት ገልጸዋል፡፡
እንደ ፊንላንድ ሁሉ የጎረቤት ሀገር ስዊድን ወደ ጥምረቱ መቀላቀል ወሳኝ መሆኑም ተናግረዋል፡፡
ሶስቱ ሀገራት ለጉዳዩ መፍትሄ ለማበጀት የሚስችሉ የሶስትዮሽ ድርድር ለማድረግ ባለፈው አመት በማድሪድ ከስምምነት መድረሳቸው አይዘነጋም፡፡
ይሁን እንጅ የፊንላንድን ጥያቄ ለማጸደቅ ሂደት የጀመረችው አንካራ የስዊድንን ጉዳይ በይደር እንደምታቆው አስታውቃለች፡፡
ቱረክ፤ የስዊድንን ጥየቄ ማቆየት ያስፈለገው ሀገሪቱ ለአንካራ የገባቸውን ቃል በመፈጸሙ ረገድ አሁንም ክፍተቶች ስላሉ ነው ብላለች፡፡
ኤርዶጋን ከኔቶ ዋና ጸሃፊ ጄንስ ስቶልተንበርግ ጋር በስልክ በነበራቸው ስልክ ቆይታመ ቱርክ አሁንም ከስዊድን ጋር ለመደራደር ዝግጁ መሆኗ ገልጸዋል ሲል ሮይተርስ የቱርክ ፕሬዝዳንት ጸ/ቤት መረጃን ጠቅሶ ዘግቧል፡፡