የትግራይ ክልል ክለቦች ከ2017 ጀምሮ ከጦርነቱ በፊት ወደነበሩበት ሊግ እንዲመለሱ እግር ኳስ ፌደሬሽን ወሰነ
የትግራይ ክልል ክለቦች የከፍተኛ ሊግ እና የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ ተሳትፋቸው የተቋረጠው ጥቅምት 2013 ወደ ጦርነት መቀስቀሱን ተከትሎ ነበር
ፌደሬሽኑ ይህን ውሳኔ ያሳለፈው የባህል እና ስፖርት ሚኒስቴር ክለቦቹ ከጦርነቱ በፊት ወደነበሩበት ሊግ እንዲገቡ ያቀረበውን ጥያቄ በመቀበል መሆኑን ገልጿል
የትግራይ ክልል ክለቦች ከ2017 ጀምሮ ከጦርነቱ በፊት ወደነበሩበት ሊግ እንዲመለሱ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ወሰነ።
ፌደሬሽኑ በዛሬው እለት በፌስቡክ ገጹ ባወጣው መግለጫ የትግራይ ክልል እግር ኳስ ክለቦች ከ2ዐ17 ጀምሮ ከጦርነቱ በፊት ወደነበሩበት ሊጎች ገብተው እንዲወዳደሩ መወሰኑን አስታውቋል።
የትግራይ ክልል ክለቦች የከፍተኛ ሊግ እና የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ ተሳትፋቸው የተቋረጠው ክልሉን የሚያስተዳድረው ህወሓት እና የፌደራል መንግስት ጥቅምት 24፣2024 ወደ ጦርነት መግባታቸውን ተከትሎ ነበር።
ጦርነቱ በፕሪቶሪያ በተፈረመው የዘላቂ ሰላም ስምምነት ከተቋጨ በኋላ የፌደራል መንግስት ለክልሉ አቋርጧቸው የነበሩ በርካታ አገልግሎቶችን አስጀምሯል።
ፌደሬሽኑ ይህን ውሳኔ ያሳለፈው የባህል እና ስፖርት ሚኒስቴር ክለቦቹ ከጦርነቱ በፊት ወደነበሩበት ሊግ እንዲገቡ ያቀረበውን ጥያቄ በመቀበል መሆኑን ገልጿል።
ፌደሬሽኑ እንዳለው የእግርኳስ ፌደሬሽን ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ፣ ክለቦች ሁለት አመት ሳይወዳደሩ ከቆዩ ሙሉ ለሙሉ ይሰረዛሉ የሚል መመሪያ ቢኖርም አንድ ደረጃ ዝቅ ብለው እንዲወዳደሩ በማለት ቀደም ብሎ ውሳኔ አሳልፎ ነበር።
ይሁን እንጂ ፌደሬሽኑ ውሳኔውን በመሻር ከጦርነት በፊት ወደነበሩበት እንዲመለሱ ወስኗል።
ፌደሬሽኑ ሊጉን "በ2017 የወድድር ዘመን በ19 ቡድኖች መካከል ውድድር ተደርጎ 5 ቡድኖች ወደ ከፍተኛ ሊግ እንዲወርዱ በማድረግ በ2018 ወደነበነረበት 16 ክለቦች እንዲመልስ" ለፕሪሚየር ሊግ አ/ማ በደብዳቤ ማሳወቁን ገልጿል።
ፌደሬሽኑ እንደገለጸው ውሳኔውን የከፍተኛ ሊግ እና አንደኛ ሊግም ተግባራዊ እንዲያደርጉት አቅጣጫ ተቀምጧል።