ሽመልስ በቀለ አሁን ላይ ለመቻል እግር ኳስ ክለብ በመጫወት ላይ ይገኛል
ሽመልስ በቀለ ራሱን ከብሔራዊ ቡድን ጨዋታዎች አገለለ
ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን እና ለስምንት የሀገር ውስጥ እና የውጭ ክለቦች የተጫወተው ሺመልስ በቀለ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ራሱን እንዳገለለ አስታውቋል፡፡
ተጫዋቹ በማህበራዊ ትስስር ገጾቹ ላይ እንደገለጸው ራሱን ከዋልያዎቹ እንዳገለለ ጽፏል፡፡
ባሳለፍነው ዓመት ከግብጽ በመመለስ ለቀድሞው መከላከያ ወይም ለአሁኑ መቻል እግር ኳስ በመጫወት ላይ ይገኛል፡፡
ላለፉት 15 ዓመታት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ቁልፍ ተጫዋች የነበረው ሽመልስ በቀለ “ጊዜው አሁን እንደሆነ ይሰማኛል ፣ ብሔራዊ ቡድኑን የምሰናበትበት ወቅት የምወደውን እና የምጓጓለትን አረንጓዴ ፣ ቢጫ እና ቀዩን ሰንደቅ አላማ ወክዬ የምጫወትበት ጊዜ እንዳበቃ ይሰማኛል። ከትልቅ አክብሮት ጋር የብሔራዊ ቡድን ጉዞዬን እዚህ ጋር ለማብቃት ወስኛለሁ” ብሏል፡፡
በሐዋሳ ከነማ ክለብ እግር ኳስን መጫወት የጀመረው ሽመልስ በቀለ በሰሜን አፍሪካዎቹ ሊቢያ ግብጽ ክለቦች ተጫውቶ ውጤታማ መሆኑን ተናግሯል፡፡
ሽመልስ ከሀገር ውስጥ ደግሞ ከልጅነት ክለቡ ሐዋሳ ከነማ በመጀመር በቅዱስ ጊዮርጊስ ዋንጫዎችን ማሸነፍ የቻለ ሲሆን ከግብጽ ቆይታው በኋላ ደግሞ ለመቻል ክለብ በመጫወት ላይ ይገኛል፡፡
አሊተሀድ ፣ ኤልሜሪክ ፣ፔትሮጀክት ፣ ኤልጉና ፣ ምስር ኤልመካሳ እና ኤን ፒፒ እግር ኳስ ክለቦች ሽመልስ በቀለ በግብጽ እና ሊቢያ የተጫወተባቸው የውጭ ሀገራት ክለቦች ናቸው፡፡
ተጫዋቹ የክለብ ጓደኞቹን፣ አሰልጣኞችን እና ደጋፊዎችን በእግር ኳስ ህይወቱ ለነበራቸው ድጋፍ ያመሰገነ ሲሆን ኢትዮጵያ ከሰላሳ አንድ ዓመታት በኋላ ለአፍሪካ ዋንጫ ስታልፍ የቡድን አባል መሆኔ ትልቁ ኩራቱ እንደሆነ እና ኢትዮጵያ ለዓለም ዋንጫ ማለፍ አለመቻሏ ደግሞ እንደሚቆጨውም ሽመልስ ጠቅሷል፡፡
ሽመልስ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን 83 ጨዋታዎችን በማድረግ 16 ጎሎችን ሲያስቆጥር 13 ለግብ የሚሆኑ ኳሶችን ማቀበሉ ይታወቃል፡፡