የኖቤል ሽልማት አሸናፊዋ የቀድሞዋ የምያንማር መሪ ከእስርቤት ወደ ቁም እስር ተዛወሩ
የዓለም መሪዎች እና የዲሞክራሲ ተሟጋቾች ሱ ቺ ከእስር እንዲለቀቁ በተደጋጋሚ ጥሪ አቅርበዋል
ኦንግ ሳን ሱ ቺ ከእስር ቤት ወደ ቁም እስር የተዛወሩት በሙቀት መጠን መጨመር ምክንያት ነው ተብሏል
የኖቤል ሽልማት አሸናፊዋ የቀድሞዋ የምያንማር መሪ ከእስርቤት ወደ ቁም እስር ተዛወሩ።
ታስረው የነበሩት ቀድሞዋ የምያንማር መሪ እና የኖቤል የሰላም ሽልማት አሸናፊዋ ኦንግ ሳን ሱ ቺ ከመደበኛ እርቤት ወጥተው የቁም እስረኛ መደረጋቸውን የወታደራዊው መንግስት ቃል አቀባይ ተናግረዋል።
የጁንታው ቃል አቀባይ ሜጀር ጀነራል ዛው ሚን ቱን "የአየር ሙቀቱ በጣም ከፍተኛ በመሆኑ ለኦንግ ሳን ሱ ቺ ብቻ ሳይሆን... ሌሎች ጥንቃቄ የሚያስፈልጋቸው በእድሜ የገፉ እስረኞችም በሙቀት እንዳይጎዱ ለማድረግ እየሰራን ነው" ብለዋል።
ሳን ሱ ቺ ወዴት እንደተዛወሩ ግን የታወቀ ነገር የለም።
የቀድሞው ጁንታ ኦንግ ሳን ሱ ቺን በያንጎንስ እንያ ሀይቅ ዳር በሚገኘው ቤተሰባዊ ቤት ውስጥ ለ15 አመታት ያህል የቁም እስረኛ ተደርገው ነበር።
የ78 አመቷ ሱ ቺ ከ2ዐ21 ጀምሮ በመንግስታቸው ላይ መፈንቅለ መንግስት ባደረገው የማያንማር ወታደራዊ ጁንታ ነበር የታሰሩት።
ሱ ቺ በሀገር ክህደት እና የቴሌኮሙኒኬሽን ህግ መጣስ ተከሰው የ27 አመታት እስር ተፈርዶባቸዋል። ሱ ቺ የቀረበባቸውን ክስ አይቀበሉትም።
ባለፈው የካቲት ወር ልጃቸው ኪም አሪስ ሱ ቺ ብቻቸውን መታሰራቸውን እና የጤናቸው ሁኔታ እንደበፊቱ ጥሩ እንዳልሆነ ተናግሮ ነበር።
የዓለም መሪዎች እና የዲሞክራሲ ተሟጋቾች ሱ ቺ ከእስር እንዲለቀቁ በተደጋጋሚ ጥሪ አቅርበዋል።