የምያንማር ወታደራዊ ጁንታ አራት የዲሞክራሲ ተሟጋቾችን በሞት ቀጣ
የምያንማር ብሔራዊ አንድነት መንግስት ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በጁንታው ላይ እርምጃ እንዲወስድ ጠይቋል
አምነስቲ ኢንተርናሽናል “ድረጊቱ በምያንማር ያለው አስከፊ የሰብዓዊ መብት አያያዝ ማሳያ ነው” ብለዋል
የምያንማር ወታደራዊ ጁንታ “የሽብር ድርጊቶችን” ለመፈጸም ተባብረዋል በሚል የከሰሳቸውን አራት የዲሞክራሲ ተሟጋቾችን በሞት ቀጣ፡፡
ከ1980ዎቹ መገባደጃ ወዲህ የደቡብ ምስራቅ እስያ ሀገር ምያንማር ለመጀመሪያ ጊዜ የወሰደችው የግዲያ እርምጃ ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ከፍተኛ ውግዘት አስከትሏል።
በጥር እና በሚያዝያ ወር በዝግ ችሎት የሞት ፍርድ የተበየነባቸው አራቱ ሰዎች፤ ለቅጣታቸው ምክንያት የሆነው ባለፈው አመት በመፈንቅለ መንግስት ስልጣን የተቆጣጠረውን እና በተቃዋሚዎቹ ላይ ደም አፋሳሽ ርምጃ የወሰደውን ወታደራዊ ጁንታ ለመጣል ሲሞክሩ ከነበሩ ሚሊሻዎች ጋር አብረዋል በሚል እንደሆነም ነው የተገለጸው፡፡
በገዢው ጁንታ ጥላ ሰር ሆኖ ሀገሪቱን እያስተዳደረ ያለው የምያንማር ብሔራዊ አንድነት መንግስት ድረጊቱን አውግዞታል፡፡
ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በጁንታው ላይ እርምጃ እንዲወስድም ጠይቋል።
የምያንማር ብሔራዊ አንድነት መንግስት ፕሬዝደንት ጽህፈት ቤት ቃል አቀባይ ክያው ዛው ቃል አቀባይ "በጣም አዝኛለሁ ... ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ለጭካኔያቸው ሊቀጣቸው ይገባል" ብለዋል፡፡
ከተገደሉት መካከል የዲሞክራሲ ሰው የሆኑት ክያው ሚን ዩ ( ጂሚ) እና የቀድሞ የህግ ባለሙያና የሂፕ-ሆፕ አርቲስት ፍዮ ዘያ ታው እንደሚገኙበት ግሎባል ኒው ላይት የተሰኘ የምያንማር ጋዜጣ ዘግቧል።
ሌሎቹ የተገደሉት ደግሞ ህላ ማዮ አውንግ እና አውንግ ቱራ ዛው የተባሉ ዴሞክራሲ ተሟጋቾች ናቸው ተብለዋል።
በቀጠናው የመብት ተሟጋች ተቋም የሆነው አምነስቲ ኢንተርናሽናል ዳይሬክተር ኤርዊን ቫን ዴር ቦርግት “እነዚህ ግድያዎች በዘፈቀደ የሰዎችን ህይወት ማሳጣት ሌላው በምያንማር ያለው አስከፊ የሰብዓዊ መብት አያያዝ ማሳያዎች ናቸው” ብለዋል።
“አራቱ ሰዎች በወታደራዊ ፍርድ ቤት የተከሰሱት በከፍተኛ ሚስጥራዊ እና ፍትሃዊ ባልሆነ ችሎት ነው፤ በተመሳሳይ ክስ ከተፈረደባቸው ከ100 በላይ ሰዎች በሞት ፍርድ እንደሚቀጡ ስለሚታመን ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ አፋጣኝ እርምጃ መውሰድ አለበት” ሲሉም ተደምጠዋል።
በምያንማር ከዚህ ቀደም ግድያዎች ሲፈጸሙ በስቅላት ነበር።