ፖለቲካ
የምያንማር ወታደራዊ ጁንታ ለቀድሞ መሪ ሱ ኪን 'በአምስት ወንጀሎች' ምህረት አደረገ
አውንግ ሳን ሱ ኪ በ2021 በወታደራዊ መፈንቅለ መንግስት ከስልጣን ከተወገዱ በኋላ በእስር ላይ ይገኛሉ
የ78 ዓመቷ ሱ ኪ የቀረቡባቸውን ከምርጫ ማጭበርበር እስከ ሙስና የሚደርሱ ክሶችን ውድቅ አድርገዋል
የምያንማር የቀድሞ መሪ አውንግ ሳን ሱ ኪ 33 ዓመታት ከተፈረደባቸው 19 ወንጀሎች መካከል በአምስቱ ይቅርታ እንደተደረገላቸው ሮይተርስ ዘግቧል።
ይቅርታው የስድስት ዓመት የእስር ጊዜያቸውን እንደሚቀንስ የወታደራዊው መንግስት ቃል አቀባይ ዛው ሚን ቱን ተናግረዋል።
ባለፈው ሳምንት በዋና ከተማዋ ናይፒይታው ከእስር ቤት ወደ ቁም እስር የተዛወሩት የኖቤል ተሸላሚዋ፤ በ2021 መጀመሪያ ላይ ወታደራዊ መፈንቅለ መንግስት ስልጣኑን ከተቆጣጠረ በኋላ በእስር ላይ ይገኛሉ።
የ78 ዓመቷ ሱ ኪ ከምርጫ ማጭበርበር እስከ ሙስና የሚደርሱ ክሶች ቀርበውባቸው፤ በሙሉ ውድቅ በማድረግ በእነሱ ላይ ይግባኝ ሲጠይቁ ቆይተዋል።
የሮይተርስ ምንጭ ሱ ኪ እና ምህረት የተደረገላቸው የቀድሞ ፕሬዝዳንት በእስር እንደሚቆዩ ተናግረዋል። "ከቁም እስራት ነጻ አይወጡም" ሲሉ ማንነታቸውን መግለጽ ያልፈለጉት ምንጭ ተናግረዋል።
የምያንማር የነጻነት ጀግና ልጅ የሆኑት ሱ ኪ ለመጀመሪያ ጊዜ በ1989 ለቁም እስር የተዳረጉት በወታደራዊ አገዛዝ ላይ ከፍተኛ ተቃውሞ ካደረጉ በኋላ ነው።
በፈረንጆቹ 1991 ለዲሞክራሲ ላበረከቱት አስተዋጽኦ የኖቤል የሰላም ሽልማትን አሸንፈዋል።