ፈረንሳይ በአዲሱ የኮሮና ቫይረስ ዝርያ የተያዘ ሰው ማግኘቷን አስታወቀች
በሌሎች ሀገራትም በመከሰት ላይ የሚገኘው አዲሱ የኮሮና ቫይረስ ዝርያ ከቀድሞው ይልቅ በፍጥነት የሚሰራጭ ነው
ቫይረሱ የተገኘበት ግለሰብ ከብሪታንያ የገባ ነው ተብሏል
በአዲሱ የኮሮና ቫይረስ ዝርያ የተያዘ ሰው በፈረንሳይ መገኘቱን የሀገሪቱ ጤና ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡ ቫይረሱ የተገኘበት ግለሰብ ነዋሪነቱ ለንደን የሆነ ፈረንሳዊ ዜግነት ያለው ሲሆን ከሳምንት በፊት ለጉብኝት ወደ ማዕከላዊ ፈረንሳይ ቱር ያመራ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት በቤቱ ራሱን አግልሎ እንደሚገኝም ሚኒስቴሩ ይፋ አድርጓል፡፡
በቅርቡ በብሪታንያ የተከሰተው አዲሱ የኮሮና ቫይረስ ዝርያ ፣ የስርጭት መጠኑ ከነባሩ ቫይረስ እስከ 70 በመቶ ይልቃል፡፡ ይህም ማለት ቫይረሱ ከቀድሞው በላቀ ፍጥነት የመዛመት አቅም አለው፡፡
አዲሱ የኮሮና ዝርያ በደቡብ ምስራቅ እንግሊዝ መከሰቱ ከታወቀ ወዲህ በርካታ ሀገራት በብሪታንያ ላይ ድንበራቸውን በመዝጋት ላይ ናቸው፡፡ ፈረንሳይም በብሪታንያ ላይ ጠንካራ እርምጃ ከወሰዱ ሀገራት አንዷ ናት፡፡ ከብሪታንያ ወደ ፈረንሳይ ምንም አይነት የሰዎች እንቅስቃሴ እንዳይኖርም ተወስኖ የነበረ ቢሆንም ፣ ለአስቸኳይ ጉዳዮች እና ለሸቀጦች እንቅስቃሴ ብቻ የፈረንሳይ ዜጎች መንቀሳቀስ እንዲችሉ የሁለቱ ሀገራት መንግሥታት ባለፈው ማክሰኞ ስምምነት ላይ ደርሰዋል፡፡
ምርመራ በማድረግ ቫይረሱ የሌለባቸው ፈረንሳውያን ዜጎች ወደ ፈረንሳይ እንዲገቡም ተወስኗል፡፡
በትናንትናው ዕለት ቫይረሱ የተገኘበት ግለሰብ እገዳው ከመጣሉ በፊት የገባ እንደሆነ ነው የተገለጸው፡፡
አዲሱ የኮሮና ቫይረስ ዝርያ በዴንማርክ ፣ ጣሊያን ፣ ጂብራልታር ፣ ኔዘርላንድስ እና አውስትራሊያም ተከስቷል፡፡
ምንም እንኳን በፍጥነት እንደሚሰራጭ ቢታመንም ፣ አዲሱ ቫይረስ ከፍተኛ ህመም ስለማስከተሉ ወይም ክትባቶችን ስለመቋቋም እና አለመቋቋሙ እስካሁን ድረስ ምንም መረጃ የለም ስካይ ኒውስ እንደዘገበው፡፡