ማክሮን በቫይረሱ መያዛቸው ከመረጋገጡ ከአንድ ቀን በፊት ከፖርቹጋሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ጋር ተገናኝተዋል
የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን በኮሮና ቫይረስ መያዛቸውን የፕሬዚዳንቱ ጽ/ቤት ዛሬ ጠዋት ይፋ አድርጓል፡፡
ፕሬዝዳንቱ ምልክቶችን ካሳዩ በኋላ ባደረጉት ምርመራ ቫይረሱ እንደተገኘባቸው ነው ጽ/ቤቱ የገለጸው፡፡ ፕሬዚዳንቱ ከዛሬ ጀምሮ ለሰባት ቀናት ራሳቸውን አግልለው ስራቸውን እንደሚቀጥሉ ተገልጿል፡፡ ከቫይረሱ እስከሚያገግሙ ስራቸውን ከኤሊዜ ቤተመንግስት ወጥተው ራቅ ባለ ስፍራ ላይ ሆነው እንደሚሰሩ የዘ ናሺናል ዘገባ ያመለክታል፡፡
ፕሬዝዳንት ማክሮን የኮሮና ምርመራ አድርገው በቫይረሱ መያዛቸው ከመረጋገጡ ከአንድ ቀን በፊት የፖርቹጋሉን ጠቅላይ ሚኒስትር አንቶኒዮ ኮስታን ፓሪስ ላይ ተቀብለው አነጋግረዋል፡፡
ለቫይረሱ እንዴት እንደተጋለጡ የታወቀ ነገር የለም፡፡
ፕሬዝዳንቱ በቫይረሱ መያዛቸውን ተከትሎ በቅርቡ ወደ ሊባኖስ እና ወደ ሌሎች ሀገራትም ሊያደርጉ ያሰቧቸው ጉብኝቶች ተሰርዘዋል፡፡
ቫይረሱ በፍጥነት ከሚዛመትባቸው ሀገራት አንዷ የሆነችው ፈረንሳይ በዚህ ሳምንት የሰዓት እላፊ አውጃለች፡፡
ሀገሪቱ እስካሁን ከ2.4 ሚሊዮን በላይ ዜጎቿ በቫይረሱ የተያዙባት ሲሆን ከ 59 ሺህ በላይ ሞት አስተናግዳለች፡፡