የተለያዩ የአውሮፓ ሀገራት ገናን እና አዲስ ዓመትን በኮሮና እገዳ ውስጥ ሊያሳልፉ ነው
ከፕሬዝዳንት ማክሮን ጋር ስብሰባ ላይ የነበሩት የስሎቫኪያ ጠ/ሚኒስትር በኮሮና ተይዘዋል
በአውሮፓ ዋነኛ የኮሮና ተጠቂ የሆነችው ጣሊያን በተወዳጆቹ በዓላት ጠንካራ ገደብ የጣሉ ሀገራትን ተቀላቅላለች
የኮሮናቫይረስ ዳግም አገርሽቶ ክፉኛ እየተፈታተናቸው የሚገኙ የአውሮፓ ሀገራት ፣ የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት የተለያዩ አይነት የእንቅስቃሴ እገዳዎችን ጥለዋል፡፡
በአውሮፓውያን ትልቅ ቦታ የሚሰጣቸው የገና እና የአዲስ ዓመት በዓላትም በዝግ እንዲያልፉ በርካታ ሀገራት በመወሰን ላይ ናቸው፡፡
በኮሮና ሟቾች ቁጥር በአውሮፓ ቀዳሚዋ ጣሊያን የገና እና የአዲስ ዓመት ወቅቶች የእንቅስቃሴ እገዳ እንደተጣለ በዝግ እንዲያልፉ የወሰኑ ሀገራትን ጎራ ተቀላቅላለች፡፡ ሀገሪቱ እስካሁን በቫይረሱ ሳቢያ 68,000 ያህል ዜጎቿን አጥታለች፡፡
እጅግ አስፈላጊ ከሆኑ ተቋማት በስተቀር ፣ ሱቆች ፣ ሬስቶራንቶች እና መጠጥ ቤቶች በዝግ እንዲቆዩ የጣሊያን መንግስት ወስኗል፡፡ ጣሊያናውያን ከቤታቸው ወጥተው መንቀሳቀስ የሚችሉት ለስራ ፣ ለህክምና እና ለአስቸኳይ ጉዳዮች ብቻ ነው፡፡
የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ጁሴፔ ኮንቴ “እዚህ ውሳኔ ላይ መድረስ ቀላል አይደለም” ብለዋል፡፡ “በገና በዓል ወቅት የኮሮና ተጠቂዎች ቁጥር በከፍተኛ መጠን ሊጨምር እንደሚችል ባለሙያዎቻቸን በአጽንኦት ገልጸዋል” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የእገዳው ውሳኔ የተላለፈው በዚሁ ምክንያት እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ጁሴፔ ኮንቴ
በርካታ እንቅስቃሴዎችን የሚከለክለው ከባዱ የእገዳ ጊዜ በአውሮፓውያኑ ከታህሳስ 24 እስከ 27 ፣ ከታህሳስ 31 እስከ ጥር 3 እንዲሁም ከጥር 5 እስከ 6 የሚቆይ ነው፡፡
ሌሎች በርካታ የአውሮፓ ሀገራትም መሰል እገዳዎችን የጣሉ ሲሆን ለአብነትም ኔዘርላንድስ እና ጀርመን ይጠቀሳሉ፡፡
በሌላ በኩል ባለፈው ሳምንት ከፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ማክሮን ጋር በአውሮፓ ሕብረት ስብሰባ ላይ የታደሙት የስሎቫኪያው ጠቅላይ ሚኒስትር ኢጎር ማቶቪች በትናንትናው ዕለት በኮሮና መያዛቸውን ይፋ አድርገዋል፡፡ ይህን ተከትሎ የቤልጂየም ፣ የስፔን ፣ የፖርቹጋል እና የሉክሰምበርግ መሪዎችን ጨምሮ በስብሰባው ላይ የነበሩት በርካታ መሪዎች ራሳቸውን አግልለዋል ሲል ቢቢሲ ዘግቧል፡፡ ፕሬዝዳንት ማክሮን በቫይረሱ መያዛቸው ከትናንት በስቲያ ታህሳስ 8/2013 ዓ.ም ተረጋግጧል፡፡