ጀርመን በሱዳን የሚገኙ ዜጎቿን ለማስወጣት ያደረገችው ሙከራ መክሸፉን ገለጸች
በሱዳን 150 ጀርመናዊያን እንደሚገኙ የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል
በርሊን ዜጎቿን በሶስት የመንገደኞች አውሮፕላን የማስውጣት እቅድ ቢኖራትም ጦርነቱ መቀጠሉን ተከትሎ አልተሳካም ተብሏል
ጀርመን በሱዳን የሚገኙ ዜጎቿን ለማስወጣት ያደረገችው ሙከራ መክሸፉን ገለጸች፡፡
ባሳለፍነው ቅዳሜ ረፋድ ላይ በካርቱም ዙሪያ የተጀመረው የሱዳን ብሄራዊ ጦር እና ፈጥኖ ደራሽ ሀይሎች ወይም አርኤስኤፍ ጦርነት አሁንም አልቆመም፡፡
ሁለቱ ተፋላሚ ሀይሎች ስልጣን ለመቆጣጠር በሚል ጦርነት መጀመራቸው የተገለጸ ሲሆን ለ24 ሰዓታት የተኩስ አቁም ስምምነት ቢደረግም ጦርነቱ መቀጠሉ ተገልጿል፡፡
ሁለቱ ተፋላሚ ጀነራሎች ለሰብዓዊ እርዳታ በሚል ለ24 ሰዓታ ተኩስ ለማቆም ተስማምተዋል መባሉን ተከትሎ በርካታ ሀገራት ዜጎችቻውን ከሱዳን ለማስወጣት አቅደው ነበር፡፡
ከነዚህ ሀገራት መካከል ጀርመን አንዷ ስትሆን በሱዳን ለተለያዩ ተልዕኮዎች የሚኖሩ 150 ዜጎቿን ለማስወጣት ሶስት አውሮፕላን እንደላከች የሀገሪቱ ዜና ወኪል ዴር ስፔግል ዘግቧል፡፡
ይሁንና ተፋላሚ ወገኖች ጦርነቱን በመቀጠላቸው ምክንያት ወደ ካርቱም የተላኩት የጀርመን አውሮፕላኖች ግሪክ ሊያርፉ ችለዋል ተብሏል፡፡
የጀርመን ውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር የሀገሪቱ አየር ሀይል ሶስት አውሮፕላኖች በሱዳን የሚገኙ ዲፕሎማቶችን፣ ፖሊሶችን፣ የተራድኦ ድርጅት ሰራተኞችን እና ሌሎች የጀርመን ዜጎችን ለማምጣት ቢያቅድም አለመሳካቱን አስታውቋል፡፡
የእስያዋ ሀገር ጃፓንም ዜጎቿን ከሱዳን ለማስወጣት በእንቅስቃሴ ላይ መሆኗን ገልጻለች፡፡