የሱዳን ጦርነት ለምን ተቀሰቀሰ፤ የሁለቱ ተቀናቃኝ ወገኖች ፍላጎትስ ምንድን ነው?
በጀነራል መሀመድ ሀምዳን ዳጋሎ የሚመራው “ራፒድ ሰፖርት ፎርስ (አር.ኤስ.ኤፍ)” ተብሎ የሚጠራው የፈጥኖ ደራሽ ኃይል እና በሱዳን ጦር መካከል የተቀሰቀሰው ውጊያ 4ኛ ቀኑን ይዟል።
በካርቱም በተቀሰቀሰው እና አሁን ላይ በተለያዩ የሱዳን አካባቢዎች እየተካሄደ ባለው ጦርነት ከ185 በላይ ሲሞቱ፤ 1 ሺህ 400 ገደማ ሰዎች መቁሰላቸው እየተነገረ ነው።
በሱዳን ጦርነት ለምን ተቀሰቀሰ?
በሱዳን ካርቱም የተቀሰቀሰው እና አሁን ላይ በተለያዩ የሱዳን አካባቢዎች እየተካሄደ በሚገኘው ጦርነት በሀገሪቱ ወታደራዊ አመራሮች መካከል ያለው አስከፊ የስልጣን ሽኩቻ ውጤት ነው።
ጦርነቱ እየተካሄደ ያለውም በሱዳን መደበኛው የመከላከያ ሰራዊት እና “ራፒድ ሰፖርት ፎርስ (አር.ኤስ.ኤፍ)” ተብሎ የሚጠራው የፈጥኖ ደራሽ ኃይል መካከል ነው።
በሱዳን ማን ማንን እየተዋጋ ነው?
በፈረንጆቹ 2021 ከተካሄደው መፈንቅለ መንግስት በኋላ ሱዳን አሁን ላይ የጦርነት መነሻ በሆኑ ሁለት የጦር ጄነራሎች በሚመራ ሉአላዊ ምክር ቤት ስትመራ ቆይታለች፤
-ጄነራል አብዱል ፈታህ አል ቡርሃን- የሱዳን ጦር ዋና መሪ እና የሱዳን ፕሬዝዳንት
-ጀነራል መሀመድ ሀምዳን ዳጋሎ “ራፒድ ሰፖርት ፎርስ (አር.ኤስ.ኤፍ)” መሪ እና የሱዳን ምክትል ፕሬዝዳንት
ሁለቱ መሪዎች ሀገሪቱ አሁን እየተጓዘችበት ባለው አቅጣጫ እንዲሁም ስልጣንን ወደ ሲቪል አስተዳደር ለመመለስ እየተደረገ ባለው ሂደት ላይ አልተስማሙም።
ዋናው የጠባቸው መነሻም 100 ሺህ የሚሆኑ ጠንካራ “ራፒድ ሰፖርት ፎርስ (አር.ኤስ.ኤፍ)” ሰራዊትን ከሱዳን ጦር ጋር የመቀላቀል ሂደት እንዲሁም ከተቀላቀሉ በኋላ አዲስ የሚዋቀረውን ኃይል ማን ይምራ? የሚለው ነው።
ሁለቱ ተቃራኒ ኃሎች ምን ይፈልጋሉ?
ጀነራል መሀመድ ሀምዳን ዳጋሎ በፈረንጆቹ 2021 የተደረገው መፈንቅለ መንግስት ስህተት እንደሆነ እንደሚያምኑ፤ እንዲሁም ራሳቸውን እንዲሁም የሚመሩት “ራፒድ ሰፖርት ፎርስ (አር.ኤስ.ኤፍ)” ከሱዳን ህዝብ ጎን እንደሆነ እና የካርቱም አሰተዳደርን እንደሚቃወም አድርገው ያቀርባሉ።
የሱዳን ፕሬዝዳንት ጄነራል አብዱል ፈታህ አል ቡርሃን በበኩላቸው፤ የሱዳን ጦር ስልጣን በሙሉ በሙሉ የሚያስረክቡት በምርጫ ለሚመረጥ መንግስት ብቻ እንደሆነ፤ ከዚህ ውጪ ለህዝቡ እወግናለሁ የሚል አካል ስልጣን መጋራት የሚችለው አሁን ባለው ምክር ቤት ውስጥ በመካተት ብቻ እንደሆነም አሳውቀዋል።
ነገር ግን ሁለቱም ወታደራዊ ኃፊዎችም ሆኑ ደጋፊዎቻቸው ከስልጣናቸው ከተነሱ በሀብታቸው እና በተጽዕኖአቸው ላይ ምን ሊደርስባቸው እንደሚችል ስጋት ውስጥ እንደወደቁ ጥርጣሬዎች አሉ።
ሀገራት ምን እያደረጉ ነው?
ጦርነቱ ሀገሪቱን የበለጠ ሊበታተን፣ የፖለቲካ ውዥንብርን ሊያባብስ እንዲሁም በአጎራባች ሀገራትንም ወደ ጦርነት ሊያስገባ ይችላል የሚል ስጋት አለ።
ሀገሪቱ ወደ ሲቪልአስተዳደር እንድትመለስ ጥረት ሲያደርጉ የነበሩ ዲፕሎማቶች ሁለቱ ጄነራሎች ተገናኝተው የሚያወሩበትን ሁኔታ ለማመቻቸት ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛሉ።
የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት (ኢጋድ) የኬንያ፣ የደቡብ ሱዳን እና የጂቡቲ መሪዎችን ወደ ካርቱም ለመላክ ውሳኔ አሳልፏል፤ ነገር ግን ወደ ሀገሪቱ የአውሮፕላን በረራዎች እየተደረጉ ባለመሆኑ መቼ እንደሚጓዙ በግልጽ አልታወቀም።
ኢትዮጵያ፣ የተባበሩት አረብ ኢምሬትስ፣ አሜሪካ፣ ብሪታኒያ፣ የፍሪካ ህብረት፣ የአውሮፓ ህብረት እንዲሁም ሌሎች ሀገራት እና ዓለም አቀፍ ተቋማት በአፋጣኝ ተኩስ አቁም እንዲደረግ እና ንግግር እንዲጀመር እያሳሰቡ ነው።