በሱዳን እየተካሄደ ባለው ጦርነት ማን ምን ተቆጣጠረ?
በሱዳን ጦር እና በጀነራል ሀምዳን ደጋሎ በሚመራው የፈጥኖ ደራሽ ኃይል(አርኤስኤፍ) መካከል ጦርነት እንደቀጠለ ነው
ከተጀመረ አምስተኛ ቀኑን ባስቆጠረው ጦርነት አንደኛቸው በሌላኛቸው ላይ ድል መቀዳጀታቸውን በመግለጽ ላይ ናቸው
በሱዳን ጦር እና በጀነራል ሀምዳን ደጋሎ በሚመራው የፈጥኖ ደራሽ ኃይል(አርኤስኤፍ) መካከል ጦርነት እንደቀጠለ ነው።
ከተጀመረ አምስተኛ ቀኑን ባስቆጠረው ጦርነት አንደኛቸው በሌላኛቸው ላይ ድል መቀዳጀታቸውን በመግለጽ ላይ ናቸው።
ሁለቱ ተፋላሚ ወገኖች የተለዩ ተቋማትን መቆጣጠራቸው እየገጹ ነው።
የፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች እያደረጉ ባለው ጦርነት የሱዳን ቤተመንግስትን፣ የካርቱምን አለምአቀፍ አየርመንገድ፣ በኦሞዱርማን የሚገኘውን የሬዲዮ እና ቴሌቪዥን ድርጅት ጨምሮ ሌሎች አየርመንገዶችን መቆጣጠራቸውን ገልጸዋል።
ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ የሜረዌ አየርመንገድንም መቆጣጠሩን አስታውቋል።
የሱዳን ጦር በበኩሉ የሬድዮና ቴሌቪዥን ጣቢያው በቁጥጥሩ ስር መሆኑን እና የፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች ስር ነው የሚለውን አስተባብሏል።
የሱዳን ጦር፣የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉን ዋና ማዘዣ ጣቢያ መያዙን እና ሌሎች ካምፖቹን መምታቱን ማስታወቁ ይታወሳል።
የጦሩ ቃል አቀባይ በዛሬው እለት ጠቅላላ ሁኔታው ጥሩ የሚባል መሆኑን እና በጠቅላይ እዙ እና በአየርመንገዱ ዙሪያ ያሉ ቦታዎችን ለመያዝ እንቅስቃሴ መኖሩን ተናግረዋል።
በአንድ ወቅት አጋር በሆኑት በሱዳን ጦር አዛዥ ጀነራል አል ቡርሃን እና ፈጥኖ ደራሽ ኃይልን በሚመሩት በጀነራል ሀምዳን ደጋሎ መካከል የተፈጠረው ግጭት ካርቱምን ወደ ጦር ሜዳነት ቀይሯታል።
በካርቱም የተለያዩ ማዕዘናት በሁለቱ ሀይሎች መካከል ጦርነቱ እየተካሄደ ይገኛል።
በትናንትናው እለት በአሜሪካ ግፊት አማካኝነት ለ24 ሰአታት ተኩስ ለማቆም ተስማምተው የነበረ ቢሆንም ተግባራዊ ሳይሆን ቀርቷል።
ተመድ በጦርነቱ እስካሁን 185 ሰዎች መገደላቸውን ገልጿል።
ሱዳንን ከሶስት አስርት አመታት በላይ ሲመሩ የነበሩት ኡሙር ሀሰን አልበሽር በህዝባዊ አመጽ ከስልጣን ከተወገዱ በኃላ ሱዳን አለመረጋጋት ውስጥ ገብታለች።
በሱዳን ስልጣን የያዘው ወታደራዊ አመራር የሲቪል መሪ የነበሩትን ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሀሞዶክን በመፈንቅለ መንግስት ከስልጣን ከስወገደ በኃላ በሱዳን ይደረጋል የተባለው የዲሞክራሲ ሽግግር ተስተጓጉሏል።