ዩክሬን በቀጣዮቹ 30 ዓመታት ውስጥ ኔቶን እንደማትቀላቀል ጀርመን ገለጸች
ሩሲያ በዩክሬን ላይ ጦርነት እንዳትጀምር ጀርመን ስታግባባ እንደነበር ተገልጿል
የሩሲያ ዩክሬን ጦርነት ከተጀመረ ዛሬ 180ኛ ቀኑ ላይ ይገኛል
ዩክሬን በቀጣዮቹ 30 ዓመታት ውስጥ ኔቶን እንደማትቀላቀል ጀርመን ገለጸች።
የጀርመኑ መራሄ ኦላፍ ሾልዝ ዩክሬን በቀጣዮቹ 30 ዓመታት ውስጥ የሰሜን አትላንቲክ ቃልኪዳን ጦር ወይም ኔቶን እንደማትቀላቀል ለፕሬዝዳንት ፑቲን እንደነገሯቸው ተገልጿል።
ኦላፍ ሾልዝ ከወራት በፊት ሞስኮን በጎበኙበት ወቅት ከፕሬዝዳንት ፑቲን ጋር ተገናኝተው በዩክሬን የጀመሩትን ጦርነት እንዲያቆሙ፣ የሩሲያን ስጋት ጀርመን እንደምትረዳ እና በሌሎች ጉዳዮች ዙሪያ መወያየታቸውን አርቲ ዘግቧል።
ሩሲያ ከዩክሬን ጋር የጀመረችውን ጦርነት እንድታቆም እና ዩክሬን በቀጣዮቹ 30 ዓመታት ውስጥ ኔቶን እንደማትቀላቀል የጀርመኑ መራሄ መንግስት ኦላፍ ሾልዝ ለፕሬዝዳንት ፑቲን ተናግረው እንደነበር ተገልጿል።
ይሁንና የሩሲያ ዩክሬን ጦርነት መቀጠሉን ተከትሎ ኦላፍ ሾልዝ ወደ ሞስኮ ማቅናታቸው ትችቶችን ያስከተለባቸው ሲሆን ዩክሬንን በሚፈለገው ልክ አኣደገፉም እየተባሉ ይገኛሉ።
ሩሲያ ለአውሮፓ ሀገራት 40 በመቶ የነዳጅ ፍላጎታቸውን የምታቀርብ ሲሆን በዩክሬን ጦርነት ምክንያት የሩሲያ ነዳጅ እንደ ቀድሞው መቅረብ አለመቻሉን ተከትሎ ጀርመንን ጨምሮ በርካታ ሀገራት ተጎድተዋል።
በጀርመን፣ ብሪታንያ፣ ቤልጂየም፣ ፈረንሳይ እና ሌሎች ሀገራት ያሉ ሰራተኞች ጦርነቱን ተከትሎ የኑሮ ውድነት ተከስቷል በሚል የደመወዝ ማስተካከያ እንዲደረግላቸው መንግስቶቻቸውን በመጠየቅ ላይ ናቸው።
የብሪታንያው ፌሊክስቶው ወደብ ሰራተኞች ለስምንት ቀናት የሚቆይ የስራ አድማ በትናንትናው ዕለት ጀምረዋል።
በብሪታንያ ሰራተኞች የደመወዝ ጭማሪ እንዲደረግላቸው በአድማ ሲጠየቅ የአሁኑ የመጀመሪያው ያልሆነ ሲሆን፤ ከዚህ በፊት የባቡር ትራንስፖርት አሽከርካሪዎች ከአንድ ወር በፊት ተመሳሳይ ነገር አድርገው ነበር።
በተጨማሪም ትምህርት ቤቶች ወጪያቸውን ለመቀነስ በሚል የትምህርት ቀናትን አሁን ካለበት ወደ ሶስት ቀናት ዝቅ ለማድረግ ምክክር መጀመራቸው ባሳለፍነው ሳምንት የወጡ ዘገባዎች ያስረዳሉ።
የጀርመኑ ግዙፍ የአቪየሽን ኩባንያ ሉፍታንዛ ሰራተኞች ደመወዝ እንዲጨመርላቸው በጠሩት የስራ ማቆም አድማ ከአንድ ሺህ በላይ በረራዎቹን መሰረዙ አይዘነጋም።