ሰባት ሀገራት እስካሁን ሁለቱ ሀገራት የኔቶ አባል እንዲሆኑ አልፈረሙም ተብሏል
የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅትን (ኔቶ) ለመቀላቀል ሂደት ላይ ያሉት ስዊድን እና ፊንላንድ በቅርቡ አባል እንደሚሆኑ ጀርመን ገለጸች።
የጀርመኑ መራሔ መንግስት ኦላፍ ሾዝ ሁለቱ ሀገሮች የድርጅቱ አባል ለመሆን የጀመሩት ሂደት በቅርቡ እንደሚጠናቀቅ እርግጠኛ መሆናቸውን አስታውቀዋል። መራሔ መንግስቱ ይህ ነው የሚል ቁርጥ ያለ ቀን ባያስቀምጡም ሀገራቱ ግን በቅርቡ ግን የኔቶ አባል እንደሚሆኑ "በራሴ እተማመናለሁ" ብለዋል።
የጀርመኑ መራሔ መንግስት ይህንን የተናገሩት ለስዊድን መሪ እንደሆነም ተገልጿል።
ሁለቱ ሀገራት የኔቶ አባል እንዲሆኑ አሜሪካ እና ፈረንሳይን ጨምሮ 23 ሀገራት አጽድቀዋል። የቀሩት ሰባት ሀገራትም በቅርቡ እንደሚፈርሙ እርግጠኛ ነኝ ብለዋል።
የቀሩት ሰባት ሀገራት በፍጥነት ፈርመው ሀገራቱ የኔቶ አባል ይሆናሉም ነው ያሉት።
ሀገራቱ ኔቶን እንዲቀላቀሉ እስካሁን ፊርማቸውን ካላስቀመጡት ሀገራት መካከል ቱርክ አንዷ መሆኗን ሾልዝ አንስተዋል።ቱርክ ይህንን ያላደረገችው ከሀገራቱ የምትፈልገውን እስካሁን ስላላገኘች ነው ተብሏል።
ቱርክ ሀገራቱ የኔቶ አባል መሆናቸውን እንደምትቃወም ቀድማ ገልጻ ነበር። በኋላ ላይ በተደረገው ውይይት ቱርክም ተስማምታ ነበር።
የስዊድን ጠቅላይ ሚኒስትር አንደርሰን ፤ ለጀርመኑ መራሔ መንግሥት ምስጋና አቅርበዋል። ጀርመን ፤ ሌሎች ሀገራት ወደ ተቋሙ እንዲገቡ እያደረገች ያለው ጥረት ምስጋና የሚገባው ነው ሲሉም ነው የስዊድን ጠቅላይ ሚኒስትር የገለጹት።
ጀርመን ኔቶን የተቀላቀለችው የሁለተኛው የዓለም ጦርነት ከተጠናቀቀ ከ 10 ዓመት በኋላ በአውሮፓውያኑ 1955 ነው። በወቅቱ ድርጅቱን የተቀላቀለችው ምዕራብ ጀርመን የነበረች ሲሆን ከምስራቅ ጀርመን የተዋሃዱት ደግሞ በአውሮፓውያኑ 1990 ነው።