ጀርመን በማሊ ያሰማራችውን ሰላም አስከባሪ ጦር ልታስወጣ መሆኗን አስታወቀች
ጀርመን በተመድ ስር በምዕራብ አፍሪካ ከተሰማራው ሰላም አስከባሪ ጦር መካከል አንዷ ነበረች
ጀርመን በባማኮ የነበራትን ሰላም ማስከበር ስራ ያቋረጠችው ማሊ ከሩሲያ ጋር መስራቷን ተከትሎ ነው
ጀርመን በማሊ ያሰማራችውን ሰላም አስከባሪ ጦር ልታስወጣ መሆኗን አስታወቀች።
የአውሮፓ ሀገራት ከዘጠኝ ዓመት በፊት በምዕራብ አፍሪካ የሽብርተኞችን ጥቃት ለመከላከል በሚል በፈረንሳይ አስተባባሪነት ለሚመራው የተመድ ሰላም ማስከበር ተልዕኮ ጦራቸው አዋጥተው ነበር።
ማሊ፣ቡርኪና ፋሶ፣ኒጀር እና ቻድ ደግሞ ከአምስት ሺህ በላይ የአውሮፓ ሀገራት ጦር የሰፈረባቸው ሀገራት ናቸው፡፡
ይሁንና በማሊ በኮለኔል አስሚ ጎይታ የሚመራው ወታደራዊ መንግስት ወደ ስልጣን ከመጣ በኋላ ምዕራባውያን ሀገራት ደስተኛ ሊሆኑ አልቻሉም።
ጀርመንም ከነዚህ ሀገራት መካከል ወነኛዋ ስትሆን የሩሲያ ቅጥረኛ ወታደሮች በማሊ መታየታቸውን ተከትሎ ወታደሮቿን ከማሊ ለማስወጣት መወሰኗን የጀርመን ድምጽ ዘግቧል።
የጀርመን መከላከያ ሚኒስትር ክሪስቲን ላምምበርችት እንዳሉት ከምንም በላይ የወታደሮቻችን ደህንነት ቅድሚያ የሚሰጡት ጉዳይ መሆኑን ተናግረዋል ።
ጀርመን ከአንድ ወር በፊት 60 ወታደሮቿን ከማሊ ያስወጣች ሲሆን የማሊ ወታደራዊ መንግሥት እያደረገ ያለው እንቅስቃሴ ስጋት እንደደቀነባቸውም ተገልጿል።
የማሊ ወታደራዊ መንግሥት ከዚህ በፊት የምዕራባውያን ሀገራት በሰላም ማስከበር ስም በርካታ ሰራዊት መስፈራቸውን እና የማሊን ሉዓላዊነት ሊጥሱ እንደማይገባ ገልጾ ነበር
ለተመሳሳይ ተልዕኮ በሚል በማሊ በሶስት ካምፖች ሰፍሮ የነበረው የፈረንሳይ ጦር ከወራት በፊት ለቆ መውጣቱ ይታወሳል።
የፈረንሳይ ፕሬዘዳንት ኢማኑኤል ማክሮን እስካለፈው ሰኔ ወር ድረስ በምእራብ አፍሪካ አገራት ያለውን አብዛኛውን ጦር ወደ ፓሪስ የመመለስ እቅድ መያዙን ከዚህ በፊት መናገራቸውም አይዘነጋም፡፡
የአውሮፓ አገራት ሰላም አስከባሪ ጦር ወደ ሳህል ቀጠና የሚሰማራው ከምዕራብ አፍሪካ አገራት ወደ አውሮፓ በመሻገር የሽብር ድርጊቶች እንዳይፈጸሙ ያለመ ነበር ተብሏል፡፡
የማሊ እና ቡርኪናፋሶ ዜጎች ከዚህ በፊት በተለያዩ ከተሞች የፈርንሳይ ጦር አገራቸውን ለቀው እንዲወጡ የሚጠይቁ ሰላማዊ ሰልፎች ማካሄዳቸው ይታወሳል፡፡