የጀርመኑ መራሄ መንግስት ከሁለት አመት በኋላ ከፑቲን ጋር በስልክ ተወያዩ
ውይይቱ የትራምፕን መመረጥ ተከትሎ ምዕራባውንያን በሩስያ ላይ ያላቸው አቋም መለሳለሱን የሚያሳይ ነው ተብሏል
ፑቲን የድንበር ሁኔታዎችን ታሳቢ ባደረገ መልኩ ከዩክሬን ጋር ስለ ስላም ለመነጋገር ዝግጁ ነን ብለዋል
የጀርመኑ መራሄ መንግስት ኦላፍ ሾልዝ እና የሩስያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ከሁለት አመታት በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ በትላንትናው ዕለት በስልክ ተወያይተዋል፡፡
ምዕራባውያን ሩስያን ለማግለል የሚያደርጉትን ጥረት የሰበረ ነው በተባለው የስልክ ውይይት ሁለቱ መሪዎች በዩክሬን ጦርነት ማቆም እና የሰላም ሁኔታ ላይ ትኩረት አድርገው መክረዋል፡፡
በውይይቱ መራሄ መንግስት ሾልዝ ፕሬዝዳንት ፑቲን ጦራቸውን ከዩክሬን እንዲያስወጡ እና ከኬቭ ጋር ፍትሃዊ እና ዘላቂ ሰላም ለማምጣት መንገድ የሚከፍት ንግግር እንዲጀምሩ አሳስበዋል፡፡
ክሬምሊን ይፋ ባደረገው መረጃ የእንወያይ ጥያቄው የመጣው በበርሊን በኩል መሆኑን ገልጾ፤ ፕሬዝዳንት ፑቲን በዩክሬን ያለውን ጦርነት ለማስቆም የትኛውም ስምምነት የሩሲያን የደህንነት ጥያቄዎች እና አዲስ የግዛት እውነታዎችን ከግምት ውስጥ ማስገባት እንደሚኖርበት መናገራቸውን አስታውቋል፡፡
የስልክ ውይይቱን የተቃወሙት የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮልድሚር ዜለንስኪ የስልክ ጥሪው የሩስያን ፕሬዝዳንት ለማግለል እና ለማዳከም የተያዘውን እቅድ የሚጎዳ ነው ማለታቸው ተሰምቷል፡፡
ዘለንስኪ ውይይቱን ተከትሎ በሰጡት መግለጫ፤ “ከፑቲን ጋር የተደረገው የስልክ ውይይት በዩክሬን ፍትሀዊ ሰላምን ለማምጣት በሚደረገው ጥረት የሚጨምረው ምንም አይነት እሴት አይኖርም፤ በአንጻሩ ፑቲን ሲፈልጉት የነበረውን የምዕራባውያንን መገለል ለመስበር እና ከሌሎች መሪዎችም ጋር ለመነጋገር በር ከፍቶላቸዋል” ሲሉ ተናግረዋል፡፡
በተጨማሪም ውይይቱ በሁለት ሀገራት መሪዎች መካከል ከሚደረግ የስልክ ውይይት ያለፈ ትርጓሜ ያለው ነው ያሉ አውሮፓውያን፥ የጀርመኑን መራሄ መንግስት ድርጊት መቃወማቸውን ሮይተርስ ምንጮቹን ጠቅሶ አስነብቧል፡፡
የስልክ ጥሪው የተደረገው ዶናልድ ትራምፕ ቀጣዩ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ሆነው ከተመረጡ በኋላ ነው፡፡
አሜሪካን ጨምሮ ምዕራባውንያን ለዩክሬን የሚያደርጉትን የጦር መሳርያ ድጋፍ የሚነቅፉት ተመራጩ ፕሬዝዳንት በጦርነቱ ኬቭ የትኛውም አይነት ጦር መሳርያ ቢሰጣት ሩስያን አታሸንፍም ብለው ያምናሉ፡፡
ከዚህ ቀደም በምርጫ ቅስቀሳቸው ወቅት በነበራቸው ንግግርም “ዩክሬን ጦርነቱን ታሸንፋለች ተብሎ የሚደረገው ወታደራዊ ድጋፍ ኪሳራ ነው፤ ከዚህ ይልቅ ከሞስኮ ጋር ስለምትደራደርበት ሁኔታ በጊዜ መነጋጋገር ይሻላል” ማለታቸው የሚታወስ ነው፡፡
ትራምፕ በዩክሬን እና ሩስያ ጦርነት ላይ የሚከተሉት ፖሊስ ከባይደን አስተዳደር እና ከምዕራባውያን አጋሮቻቸው ፖሊሲ እንደሚለይ በተለያየ መንገድ አሳይተዋል፡፡
የትላንቱ የስልክ ውይይትም የዶናልድ ትራምፕን መመረጥ ተከትሎ ምዕራባውንያን በሩስያ ላይ ያላቸው አቋም መለሳለሱን የሚያሳይ ነው ተብሏል፡፡
ጀርመን "ሊዮፓርድ 2" የተሰኘውን ታንክ ለዩክሬን መላኳና የሩሲያን ዲፕሎማቶች ማባረሯ ከሞስኮ ጋር ግንኙነቷን አሻክሮት መቆየቱ ይታወሳል።