ትራምፕ እና ፑቲን በስልክ ተወያዩ የሚለው መረጃ ሀሰት ነው ሲል ክሬሚሊን አስተባበለ
ዋሽንግተን ፖስት ሁለቱ መሪዎች በነበራቸው ቆይታ በዩክሬን ጉዳይ ላይ አተኩረው መክረዋል ሲል ዘግቦ ነበር
የክሬሚሊን ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ መሪዎቹ ተወያይተዋል ተብሎ የተሰራጨው መረጃ ሀሰተኛ ነው ብለዋል
ትራምፕ እና ፑቲን በስልክ ተወያዩ የሚለው መረጃ ሀሰት ነው ሲል ክሬሚሊን አስተባበለ።
ተመድ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር በትላንትናው ዕለት በስልክ ተወያይተዋል የሚል ዘገባ ወጥቶ ነበር።
የስልክ ውይይቱ በዩክሬን ላይ ያተኮረ መሆኑን ትራምፕ ፑቲን የዩክሬንን ጦርነት ከማባባስ እንዲቆጠቡ ማሳሰባቸውን የሚል ነበር ዘገባው።
ሁለቱ መሪዎች መወያየታቸውን የሚጠቅሱ ዘገባዎች በሮይተርስ እና ዋሽግተን ፖስት ከተሰራጩ በኋላ ክሪምሊን መረጃው ሀሰት ነው ሲል አስተባብሏል፡፡
ቃል አቀባዩ ዲሚትሪ ፔስኮቭ “ፑቲን ባለፈው ሳምንት ከአዲሱ የአሜሪካ አስተዳደር ጋር በቅርበት ለመስራት ፍላጎት እንዳላቸው ከመናገራቸው ውጭ ከትራምፕ ጋር በስልክ እንደተወያዩ የተዘገበው ዜና ሀሰተኛ ነው” ብለዋል፡፡
በትራምፕ እና በፑቲን መካከል ስለተደረገው የስልክ ውይይት አስቀድሞ መረጃው እንደሌለው የገለጸው የዩክሬን የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር በበኩሉ ተደርጓል የተባለውን ውይይቱን ከመደገፍም ከመቃወምም ተቆጥቧል፡፡
የትራምፕ የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር ስቲቨን ቼንግ ስለተደረገው የስልክ ጥሪ በዋሽንግተን ፖስት ተጠይቀው "በፕሬዚዳንት ትራምፕ እና በሌሎች የዓለም መሪዎች መካከል በሚደረጉት የግል ጥሪዎች ላይ አስተያየት አንሰጥም" ብለዋል ።
ለዩክሬን የሚሰጠውን የገንዘብ እና ወታደራዊ ድጋፍ መጠን አጥብቀው የሚተቹት ትራምፕ ባሳለፍነው እሮብ ከዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮልደሚር ዘለንስኪ ጋር በተመሳሳይ ውይይት አድርገው ነበር፡፡
ከተመራጩ ፕሬዝዳንት ጋር ለመወያየት ግብዣ ያቀረቡት ጆ ባይደን ከነገ በስቲያ “በኦቫል ኦፊስ” በሚኖራቸው ንግግር ትራምፕ ዩክሬንን እንዳይተዋት ድጋፉንም አጠናክረው እንዲቀጥሉ ይጠይቋቸዋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
የአሜሪካ የብሔራዊ ደህንነት አማካሪ ጄክ ሱሊቫን ባይደን ሰላማዊ የስልጣን ሽግግርን ለማረጋገጥ ቁርጠኛ መሆናቸውን እና በአውሮፓ ፣ በእስያ እና በመካከለኛው ምስራቅ ስላለው ሁኔታ ከትራምፕ ጋር እንደሚነጋገሩ ገልጸዋል።
አማካሪው ይህን ባሉበት ቀን ዩክሬን ጦርነቱ ከተጀመረ አንስቶ ግዙፉ የተባለውን የድሮን ጥቃት በሞስኮ ላይ ፈጽማለች፡፡
ተሰናባቹ ፕሬዝዳንት በስልጣን ላይ በሚኖራቸው 70 ቀናት ውስጥ ጉዳዩን ወደ ኮንግረሱ በመውሰድ አዲሱ አስተዳደር ኪቭን ፈጽሞ ሊተዋት እንደማይገባ ይህ የሚሆን ከሆነ በአውሮፓ የበለጠ አለመረጋጋትን ሊያስከትል እንደሚችል ለማስረዳት የሚጥሩ ይሆናል፡፡
ጄክ ሱሊቫን ባይደን ለዩክሬን ቀጣይነት ያለው ድጋፍ እንዲደረግ ኮንግረሱ ህግ እንዲያወጣ ሊጠይቁ እንደሚችሉ ተጠይቀው "እኔ እዚህ የመጣሁት የተለየ የህግ ፕሮፖዛል ለማቅረብ አይደለም፤ የማውቀው ፕሬዝዳንት ባይደን በስልጣናቸው ማብቂያ ለዩክሬን ቀጣይነት ያለው ድጋፍ እንደሚያስፈልግ ጉዳዩን እንደሚያቀርቡ ብቻ ነው" ሲሉ መልሰዋል፡፡
በባይደን አስተዳደር ኮንግረሱ ከ174 ቢሊዮን ዶላር በላይ ለዩክሬን ሰጥቷል፤ ሪፐብሊካኖች የሀገሪቱን ሴኔት 52 መቀመጫዎችን በመያዝ የበላይ መሆናቸውን ተከትሎ የእርዳታው መጠን በትራምፕ አስተዳደር ሊቀንስ እንደሚችል ይጠበቃል፡፡