ጀርመን የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን ለሚገዙ ሰዎች 6 ሺህ ዩሮ ቦነስ እንደምትከፍል ገለጸች
ያገለገሉ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን ለሚገዙ ደግሞ 3 ሺህ ዩሮ ይከፈላቸዋል ተብሏል
የጀርመን ሀይል እና ውሃ ኢንዱትሪ ማህበር ግን መጀመሪያ ቻርጅ ማድረጊያ መሰረተ ልማቶች እንዲስፋፉ ጠይቋል
ጀርመን የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን ለሚገዙ ሰዎች 6 ሺህ ዩሮ ቦነስ እንደምትከፍል ገለጸች፡፡
የአውሮፓ ግዙፍ ኢኮኖሚ ባለቤት የሆነችው ጀርመን በኤሌክትሪክ የሚሰሩ ተሽከርካሪዎችን ለማበረታታት የተለያዩ አሰራሮችን በመዘርጋት ላይ መሆኗን አስታውቃለች፡፡
አሽከርካሪዎች በነዳጅ የሚሰራ ንብረታቸውን ወደ ኤሌክትሪክ ከቀየሩ የገንዘብ ሽልማት መክፈል አንዱ ማበረታቻ ሲሆን በተለይም አዲስ የኤሌክትሪክ መኪና ለሚገዙ ሰዎች 6 ሺህ የሮ የቦነስ ክፍያ እንዲከፈላቸው የሚፈቅድ ህግ ተዘጋጅቷል፡፡
በተጨማሪም ያገለገሉ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን የሚገዙ ደግሞ ሶስት ሺህ ዩሮ እንዲከፈላቸው አዲስ የተዘጋጀው ረቂቅ ህግ ይፈቅዳል፡፡
በጀርመን ሶሻል ዲሞክራቲክ ፓርቲ የተዘጋጀው ይህ ረቂቅ ህግ ሀገሪቱ የገጠማትን የአየር ብክለት ለመቀነስ ያለመ እንደሆነም ተገልጿል፡፡
በጀርመን የነዳጅ ተሽከርካሪዎች ለአየር ብክለት የ20 በመቶ አስተዋጽኦ አላቸው የተባለ ሲሆን አዲሱ ህግ ይህንን ለመቀልበስ ተብሎ የተዘጋጀ እንደሆነ ዩሮ ኒውስ ዘግቧል፡፡
ይሁንና የጀርመን ሀይል እና ውሃ ኢንዱትሪ ማህበር ረቂቅ ህጉን የተቃወመ ሲሆን መንገስት መጀመሪያ ላይ ለኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች የሚያስፈልጉ መሰረተ ልማቶችን እንዲያሟላ ጠይቋል፡፡
ማህበሩ አክሎም ሰዎች የገንዘብ ማበረታቻውን ለማግኘት ሲሉ በነዳጅ የሚሰሩ ተሽከርካሪዎቻቸውን ወደ ኤሌክትሪክ ቢቀይሩ ሊገለገሉ የሚችሉባቸው እንደ ቻርጀር፣ የኤሌክትሪክ ባትሪ እና ተያያዥ መሰረተ ልማቶች እጥረት ሊያጋጥም እንደሚችልም አስጠንቅቋል፡፡
በአውሮፓ ዋንጫ ምክንያት በጀርመን የከተሙት 100 ሺህ ሴተኛ አዳሪዎች ከየት የመጡ ናቸው?
አስፈላጊ መሰረተ ልማቶች ሳይሟሉ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች በገፍ ቢጥለቀለቁ ኢንዱትሪውን ሊጎዳው እንደሚችልም ተገልጿል፡፡
ጀርመን በ2045 በነዳጅ ከሚሰሩ ተሽከርካሪዎች የሚለቀቅ በካይ ጋዝ መጠንን ዜሮ ለማድረስ ያስቀመጠችው እቅድ አሁን ባላት ፍጥነት ከቀጠለ እቅዱ አይሳካም ተብሏል፡፡
ሀገሪቱ ለዚህ እቅድ 5 ቢሊዮን የሮ በጀት እንደምትመድብ የገለጸች ሲሆን ረቂቅ ህጉ ከጸደቀ እና ወደ ትግበራ ከገባ ከሁለት ሚሊዮን በላይ የነዳጅ መኪኖች ወደ ኤሌክትሪክ እንዲቀየሩ ምክንያት ይሆናል፡፡
እንዲሁም የገንዘብ ማበረታቻው የመኪና ሽያጭ ንግዱን በ28 በመቶ ተጨማሪ እድገት እንዲኖረው ያስችላልም ተብሏል፡፡