ጀርመን፤ የሩሲያ ጋዝ ወደ ሀገሯ በበቂ ሁኔታ ካልገባ ኢንዱስትሪዎች ሊዘጉ ይችላሉ ስትል አስጠነቀቀች
ሩሲያ፤ 40 በመቶ የአውሮፓ ሀገራትን የነዳጅ ፍላጎት ታሟላ ነበር
ጀርመን ማዕቀብ ሳትጥስ በሩሲያ መገበያያ ገንዘብ ነዳጅ ለመግዛት መስማማቷ ይታወሳል
በጋዝ እጥረት ምክንት ኢንዱስትሪዎች ሊዘጉ እንደሚችሉ የጀርመን ኢንዱስትሪ ሚኒስትር አስጠነቀቁ።
ሚኒስትሩ ሮበርት ሃቤክ ለሀገራቸው ጋዜጣ ዴርስፔግል እንዳሉት የሩሲያ ጋዝ በበቂ ሁኔታ ወደ ሀገራቸው ካልመጣ ኢንዱስትሪዎች ስራ ሊያቆሙ ይችላሉ ብለዋል።
አሁን ላይ ከሩሲያ ወደ ጀርመን የሚመጣው ጋዝ አነስተኛ እንደሆነ ያነሱት ሚኒስትሩ አቅርቦቱ በዚህ መጠን ከቀጠለ ሁኔታው አስቸጋሪ ሊሆን እንደሚችል ገልጸዋል፡፡
የሩሲያ ነዳጅ ወደ ጀርመን በበቂ መጠን የማይመጣ ከሆነ ኩባንያዎች ተዘግተው ሰራተኞቻቸውንም ሊበትኑ ይችላሉ ሲሉ ሚኒስትሩ ስጋታቸውን ገልጸዋል።
በሩሲያ ዩክሬን ጦርነት ምክንያት ወደ ጀርመን የሚገባው ጋዝ አነስተኛ ከሆነ ሰራተኞች ከኢንዱስትሪዎች ተሰናብተው ዕዳ ውስጥ እንደሚዘፈቁና ያንን ለመክፈል ሲሉ ብዙ መስዋዕትነት ሊከፍሉ እንደሚችሉም ሚኒስትሩ ተናግረዋል።
ሚኒስትር ሃቤክ፤ የሩሲያ ጋዝ በበቂ ሁኔታ የማይመጣ ከሆነ ኢንዱስትሪዎች ከመዘጋትም አልፈው ዜጎች ከፍተኛ ድህነት ውስጥ ይገባሉ፤ ይህ ደግሞ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጀርመንን ለመከፋፈል ያቀዱት አንድ ዘዴ ነው ብለዋል።
ይህ ሁኔታ ለሕዝበኝነት ትልቅ በር የሚከፍት መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሩ ዴሞክራሲን ሊያዳክም እንደሚችልም ሰግተዋል።
የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነትን ተከትሎ በሩሲያ ላይ ከ6 ሺህ በላይ ማዕቀቦች የተጣሉ ሲሆን ከ300 በላይ ዲፕሎማቶቿ ደግሞ ከተለያዩ ሀገራት ተባረው ወደ ሞስኮ ተመልሰዋል።
ሩሲያም የአጻፋ እርምጃ በመውሰድ ነዳጅ ገዢ ሀገራት በሩብል እንዲገዙ ውሳኔንም ያሳለፈች ሲሆን ጀርመን እና ጣልያን ማዕቀቡን ሳይጥሱ ከሩሲያ ነዳጅን በሩብል ለመግዛት ወስነው ነበር።
40 በመቶ የአውሮፓ ሀገራትን የነዳጅ ፍላጎት የምታሟላው ሩሲያ ናት።