ኢኮኖሚ
ጀርመን ዝቅተኛ የስራ ሰዓት ክፍያን ወደ 12 ዩሮ አሳደገች
አዲሱ ዝቅተኛ የስራ ሰዓት ሰራተኞች ክፍያ የፊታችን ጥቅምት ጀምሮ ስራ ላይ ይውላል ተብሏል
ጀርመን አሁን ላይ ለአንድ ሰራተኛ በሰዓት በትንሹ 10 ዩሮ በመክፈል ላይ ተገኛለች
የሰራተኞች እጥረት የገጠማት ጀርመን በየጊዜው ለሰራተኞቿ የምትከፍለውን ዝቅተኛ የስራ ክፍያ እያሳደገች የመጣች ሲሆን አሁን ደግሞ በሰዓት ዝቅተኛ የሰራተኞች ክፍያን ወደ 12 ዩሮ አሳድጋለች።
የጀርመን ህግ አውጪ ምክር ቤት እንደወሰነው በሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት ምክንያት የምርቶች ዋጋ ግሽበት በማጋጠሙ ሀገሪቱ ለሰራተኞች የሚከፈል ዝቅተኛ ክፍያን አሻሽሏል።
እንደ ሀገሪቱ ምክር ቤት ውሳኔ ከሆነ ይህ የሰራተኞች ክፍያ ማሻሻያ ከቀጣዩ ጥቅምት ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚደረግ ተገልጿል።
ጀርመን ለሰራተኞቿ በሰዓት 9 ዩሮ በመክፈል ላይ የነበረች ስትሆነ ከሶስት ቀናት በፊት ክፍያውን ወደ 10 ዩሮ ማሳደጓን አሳውቃለች።
እንዲሁም የአንድ ሰራተኛ ወርሃዊ የትርፍ ሰዓት አገልግሎት ክፍያ ከ450 ዩሮ ወደ 520 ዩሮ ማደጉ ተገልጿል።
የጀርመን ታቃዋሚ ፓርቲዎች በበኩላቸው ለሰራተኞች የተጨመረው ዝቅተኛ የስራ ሰዓት ጭማሪ ለኑሮ ውድነቱ መፍትሄ አይሆንም ሲሉ ድርጊቱን ኮንነዋል።
መፍትሄው ለሰራተኞች ደመወዝ መጨመር ሳይሆን ኢኮኖሚው የተረጋጋ ማድረግ የሚያስችሉ እርምጃዎችን መውሰድ ነው ሲሉም ፓርቲዎቹ አሳስበዋል።