የጋና ፕሬዚዳንት ናና አኩፎ አዶ በድጋሚ ተመረጡ
ዴሞክራሲያዊ ምርጫ የማድረግ ልምድ ያላት ሀገሪቱ የአሁኑን ምርጫም በስኬት ማከናወኗ በታዛቢዎች ተመስክሯል
ፕሬዚዳንት ናና አኩፎ የቀድሞውን ፕሬዝዳንት በማሸነፍ ነው ለሁለተኛ ጊዜ የተመረጡት
የተሻለ ዴሞክራሲ ካላቸው የአፍሪካ ሀገራት መካከል የምትጠቀሰው የጋና ፕሬዝዳንት ናና አኩፎ አዶ ከሶስት ቀናት በፊት የተካሔደውን ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ማሸነፋቸውን የሀገሪቱ ምርጫ ኮሚሽን አስታውቋል፡፡
በምርጫው 51.6 በመቶ ድምጽ በማግኘት 47.4 በመቶ ድምጽ ያገኙትን ዋነኛ ተቀናቃኛቸውን ጆን ድራማኒ ማሃማን ያሸነፉት የ 76 ዓመቱ ናና አኩፎ ምዕራብ አፍሪዊቷን ሀገር ለቀጣይ 4 ዓመታት መምራታቸውን ይቀጥላሉ፡፡
የተቃዋሚው ናሽናል ዴሞክራቲክ ኮንግረስ መሪ እና የሀገሪቱ የቀድሞው ፕሬዝዳንት ጆን ማሃማ ስለውጤቱ እስካሁን የሰጡት አስተያየት ባይኖርም ሀገሪቱ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ በማድረግ የማትታማ በመሆኑ አለመግባባት ሊፈጠር የሚችልበት እድል እጅግ ጠባብ እንደሆነ ይታመናል፡፡
ምርጫውን በታዛቢነት የተከታተሉት የአፍሪካ ህብረት ፣ የኢኮዋስ እና በቀጣናው የተባበሩት መንግስታት ተወካዮችም ምርጫው ሰላማዊ እና ዴሞክራሲያዊ መሆኑን በመመስከር ለጋና ህዝብ አድናቆታቸውን ቸረዋል፡፡
ምርጫውን በድጋሚ ያሸነፉት ፕሬዝዳንት ናና አኩፎ የስራ አጥነት ችግርን መቀነስ እና በኮሮና ምክንያት የተዳከመውን የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ማነቃቃት ዋነኛው ቀጣይ የቤት ስራቸው ነው፡፡
ከ1992 ፣ማለትም የመድብለ ፓርቲ ምርጫ ስርዓት ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ ጋና እስካሁን በአምስት ፕሬዚዳንቶች የተመራች ሲሆን በአፍሪካ የተረጋጋ ዴሞክራሲን ከገነቡ ሀገራት አንዷ ናት፡፡ በሀገሪቱ ቅድመ ምርጫና ድህረ ምርጫ ወቅት ግርግሮች ካለመነሳታቸውም በላይ እስካሁን የሥልጣን ሽግግሮችም ሰላማዊ በሆነ መንገድ ተከናውነዋል፡፡