ፖለቲካ
ጋናውያን ቀጣይ ፕሬዝዳንታቸውን ለመምረጥ ድምጽ እየሰጡ ነው
ጋና በአፍሪካ የተሻለ ዴሞክራሲ ካላቸው እና ተዓማኒ ምርጫ ከሚያደርጉ ጥቂት ሀገራት በቀዳሚነት ትጠቀሳለች
ፕሬዝዳንት ናና አኩፎ ከቀድሞው ፕሬዝዳት ጆን ድራማኒ ማሃማ ከፍተኛ ፉክክር ይጠብቃቸዋል
ጋናውያን አዲስ ፕሬዚዳንትና የምክር ቤት አባላትን እየመረጡ ሲሆን ድምጽ የመስጠቱ መርሃ ግብር እየተካሄደ መሆኑን ቢቢሲ ዘገቧል፡፡
ሀገሪቱ የመድብለ ፓርቲ የፖለቲካ ስርዓት ከጀመረችበት እ.አ.አ ከ 1992 ጀምሮ የአሁኑ ለስምንተኛ ጊዜ እየተደረገ ያለ ምርጫ ነው፡፡ ከ 25 ሚሊዮን በላይ ከሚሆነው ህዝቧ ውስጥ ከ 17 ሚሊዮን በላይ መራጮች ድምጽ እንደሚሰጡም ነው የሀገሪቱ ምርጫ ባለሥልጣናት ያስታወቁት፡፡
ፕሬዝዳንት ናና አኩፎ አዶ ለሁለተኛ የስልጣን ዘመን ለመመረጥ እየተወዳደሩ ሲሆን ከቀድሞው ፕሬዝዳት ጆን ድራማኒ ማሃማ ከፍተኛ ፉክክር እንሚጠብቃቸው ተዘግቧል፡፡ ጆን ድራማኒ ማሃማ ጋናን ከአውሮፓውያኑ 2012 እስከ 2017 መምራታቸው ይታወሳል፡፡
ከ1992 ፣ማለትም የመድብለ ፓርቲ ምርጫ ስርዓት ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ ጋና እስካሁን አምስት ፕሬዚዳንቶች የነበሯት ሲሆን በአፍሪካ የተሸለ ዴሞክራሲን ተግባር ላይ ካዋሉ ሀገራት አንዷ እንደሆነች ይታመናል፡፡ ለዚህ እምነት መነሻው በሀገሪቱ ቅድመ ምርጫና ድህረ ምርጫ ወቀት ግርግሮች ካለመነሳታቸውም በላይ በሀገሪቱ የተካሄዱት የሥልጣን ሽግግሮች ሰላማዊ በመሆናቸው ነው፡፡