ፕሬዘዳንት ቡሃሪ የታገቱትን ተማሪዎች ከእገታ ለማስለቀቅ ወደ ስፍራው የጸጥታ ሃይል መላካቸው ተገልጿል
በናይጀሪያ ኒጀር ግዛት ውስጥ በሚገኘ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ውስጥ ጥቃት በመፈጸም ተማሪዎችን ማገታቸው የግዛቱ ቃል አቀባይ አስታውቀዋል፡፡
ታጣቂዎቹ ትናንት ምሽት የመንግስት የሳይንስ ኮሌጅ ውስጥ በመግባት በቦታው የነበረውን የኮሌጁን የጸጥታ ኃይል መቆጣጠራቸውን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡ ቃል አቀባዩ ብዙ ተማሪዎች መታገታቸውን የገለጹ ሲሆን ምንያህል ተማሪዎች እንደታገቱ ግን አልተናገሩም፡፡
ለጥቃቱ ማን ኃላፊነት እንደሚወስድም አልታወቀም፡፡
ፕሬዘዳንት ሙሃመድ ቡሃሪ ጥቃቱን አውግዘዋል፤ የታገሩትን ተማሪዎች ከእገታ ለማስለቀቅ ወደ ስፍራው የጸጥታ ሃይል ልከዋል፡፡ የቦኮሃራም ታጣቂዎች በቦታው እንደሚንቀሳቀሱ የሚታወቅ ሲሆን በሌሎች ታጣቂዎች ተማሪዎችን ለገንዘብ መያዝ የተለመደ ነው፡፡
ይህ ጥቃት ከሁለት ወራት በፊት ታጣቂዎች በሰሜናዎ ምእራብ ካሲና ግዛት በሚገኘ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ላይ ጥቃት በመክፈት 350 ተማሪዎችን ካገቱና ወዲያውኑ ከተለቀቁበት ጥቃት የቅርብ የሚባለው ነው፡፡
ቦኮሃራም በፈረንጆቹ 2014 በቺቦክ ከተማ ከ270 ተማሪዎች 100 የሚሆኑት የታገቱ ሲሆን እስካሁን ደብዛቸው አልተገኘም፡፡ እንደዚህ አይነት ጥቃቶች በናይጀሪያ የታጣቂዎች ጥቃት አሳሳቢ እንዲሆንና በፕሬዘዳንት ቡሃሪ ላይ የተሰነዘረውን ትችት ያባብሰዋል ተብሏል፡፡ ባለፈው ጥር ፕሬዘዳንቱ አዲስ ኮማንድ ማቋቋማቸው ይታወሳል፡፡
የጸጥታ መደፍረስና አለመረጋጋት ችግር በናይጀሪያ ያለውን ኢኮኖሚያ ቀውስ እያባባሰው መሆኑ ተገልጿል፡፡