የባይደን አስተዳደር ለግብፅ የ 197 ሚሊዮን ዶላር የጦር መሳሪያ ሽያጭ አፀደቀ
የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ በግብጽ የሰብዓዊ መብት ጉዳዮችን በጥብቅ እንደሚታተል አስታውቋል
ለግብፅ የጦር መሳሪያ ሽያጭ መፅደቁ አሜሪካን በሰብዓዊ መብት ድርጅቶች እያስተቻት ነው
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ማክሰኞ ዕለት ለግብፅ ወደ 200 ሚሊዮን ዶላር የሚገመት የጦር መሳሪያ ሽያጭ ያፀደቀ ሲሆን ይህም በባይደን አስተዳደር የመጀመሪያው የመሳሪያ ሽያጭ ነው፡፡
ሽያጩ ተሽከርካሪ ሚሳይሎችን እና ተያያዥ መሣሪያዎችን ያካተተ ሲሆን ዋጋው 197 ሚሊዮን ዶላር እንደሆነ ተገልጿል፡፡
የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ቃል አቀባይ ኔድ ፕራይስ በመግለጫቸው “የጦር መሳሪያ ሽያጩ በመካከለኛው ምስራቅ የአሜሪካ ወሳኝ ስትራቴጂካዊ አጋር ሆና የምትቀጥለውን የግብፅን ፀጥታ ለማጠናከር በማገዝ ለአሜሪካ የውጭ ፖሊሲ እና ብሔራዊ ደህንነት ይጠቅማል” ብለዋል፡፡
የመሳሪያ ሽያጩ የግብፅ የባህር ኃይል ለመደገፍ እንዲሁም የሀገሪቱን ዳርቻ አካባቢዎች እና የስዊዝ ቦይ መዳረሻዎችን የመከላከል አቅምን ለማሳደግ ታስቦ የሚፈጸም እንደሆነ ነው የተጠቆመው፡፡
የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ በከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ለምትታማው ለግብፅ የጦር መሳሪያ ሽያጭ ማፅደቁ ፣ በሰብዓዊ መብት ድርጅቶች እያስተቸው ነው፡፡
ሚስተር ፕራይስ “ከግብፅ መንግስት ጋር በሰብአዊ መብት ጉዳዮች ላይ መነጋገራችንን እንቀጥላለን ፤ ያለአግባብ በቁጥጥር ስር የዋሉ ወይም የታሰሩ ሰዎችን ጉዳይ በቁም ነገር እንመለከታለን” ብለዋል ሲል ዘ ናሺናል ዘግቧል፡፡
በአሜሪካ ሕግ ኮንግረሱ ሽያጩን ለመመርመር 30 ቀናት ይኖረዋል ፤ ነገር ግን በግብይቱ ላይ የሚያሳድረው ተፅዕኖ የለም፡፡
ፕሬዝዳንት ጆ ባይደንም ይሁኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን እስካሁን ለግብፅ መሪዎች ስልክ አልደወሉም፡፡
ባለፈው ግንቦት የትራምፕ አስተዳደር 2.3 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጣ መሳሪያ ለግብፅ የማቅረብ ስምምነትን አፅድቆ ነበር፡፡