የሀላባ ብሔረሰብ የዘመን መለወጫ የሴራ በዓል በአዲስ አበባ ተከበረ
የሀላባ ብሔረሰብ የዘመን መለወጫ የሴራ በዓል ዛሬ ታህሳስ 26 ቀን 2012 ዓ.ም በአዲስ አበባ የተከበረውለመጀመሪያ ጊዜ ነው፡፡
በከተማዋ የሚኖሩ እና ከዞኑ የመጡ የብሔሩ ተወላጆች በኦሮሞ የባህል ማዕከል በአሉን ሲያከብሩ የከተማ አስተዳደሩ ምክትል ከንቲባ ኢ/ር ታከለ ኡማ ፣ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትሯ ሂሩት ካሰው (ዶ/ር)፣ የሠራተኛና ማህበራዊ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) እንዲሁም ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች በሀላባ ባህላዊ አልባሳት አሸብርቀው ታድመዋል፡፡
ኢ/ር ታከለ ኡማ በክብረ በዓሉ ላይ ባስተላለፉት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አዲስ አበባ የሁሉም ኢትዮጵያውያን የጋራ ከተማ መሆኗን በዋውሳት፣ በቀጣይ አመታት በዓሉን በተለየ ድምቀት ለማክበር አስተዳደሩ ጥረት ያደርጋል ብለዋል፡፡
በአዲስ አበባ የሚኖሩ የሀላባ ብሔረሰብ ተወላጆች በከተማዋ ሁለንተናዊ የልማት ተግባራት ጠንካራ ድጋፍ እንዲያደርጉም ምክትል ከንቲባው በአጋጣሚው ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ቀደምት ኢትዮጵያውያን እንደ ሀላባው ሴራ ያሉ ባህላዊ እሴቶችን ጠብቀው ለትውልድ ያስተላለፉት ፈታኝና አስቸጋሪ ሁኔታዎችን በጽናት በማለፍ ነው ያሉት የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትሯ ሂሩት ካሰው (ዶ/ር) ባደረጉት ንግግር ደግሞ፣ የበርካታ ማህበረሰባዊ ችግሮቻችን መፍቻ ቁልፍ የሆኑትን እነዚን ባህሎች ልንጠብቃቸው ይገባል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ዘንድሮ በአዲስ አበባ ለመጀመሪያ ጊዜ የተከበረው ሴራ በብሄረሰቡ ዘንድ በተደራጀ መልኩ ሲከበር የአሁኑ ዘጠነኛው ነው፡፡ በክብረ በዓሉ ላይ የሀላባ ባህላዊ ጭፈራዎች፣ አልባሳት እና መሰል ባህላዊ ትዕይንቶች ቀርበዋል፡፡
የሴራ በዓል በየዓመቱ በታህሳስ ወር ወይም በብሄረሰቡ አጠራር መንገሳ በሚባለው ወር የሚከበር ሲሆን፣ክብረ በዓሉ በተለያዩ ዝግጅቶች ከታህሳስ ወር መጨረሻ እስከ ጥር የመጀመሪያ ሳምንት ድረስ ይዘልቃል፡፡
በሀላባ ባህል መሰረት ሴራ ሁለንተናዊ የብሄሩ መገለጫ ሲሆን፣ እንደ ብዙ የኢትዮጵያ ብሄረሰቦች ሁሉ ለጋብቻ የደረሱ ወጣቶች የሚተጫጩበት፣ ታዳ ህጻናት የሚገረዙበት፣ እርቅ የሚፈጸምበት እና በዓሉ መሰል ማህበረሰባዊ የባህል ተግባራት የሚከናወኑበት ነው፡፡
በቅርቡ በዞን ደረጃ የተዋቀረው የሀላባ ብሄር በደቡብ ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል ውስጥ ከሚገኙ ብሄሮች አንዱ ነው፡፡