
የፈጠራ ስራውም ባለፈው አመት የ25 ሺህ ዶላር ሽልማት እንዳስገኘለት ይታወሳል
ታዋቂው ታይም መጽሄት የ15 አመቱን ትውልደ ኢትዮጵያዊ ሄማን በቀለ የ2024 “ምርጥ ህጻን” አድርጎ መርጦታል።
መጽሄቱ ሄመንን የመረጠው የተለያዩ የቆዳ ካንሰር ህመሞችን ለመከላከልና ለማከም የሚውል ሳሙና በመፍጠሩ ነው።
በአዲስ አበባ የተወለደውና በአራት አመቱ ወደ አሜሪካ ያቀናው ሄማን ከሰባት አመቱ ጀምሮ ወደ ሳይንሳዊ ሙከራዎች መሳቡን ያስታውሳል።
በቤት ውስጥ ያገኘውን ነገር ሁሉ እያደባለቀ ውጤቱን የመመልከት ፍላጎት እንደነበረውም ነው ለታይም መጽሄት የተናገረው።
ታዳጊው ገና በህጻንነቱ ሳሙናዎችን ከተለያዩ በቤት ውስጥ ከሚገኙ ኬሚካሎች ጋር ቀላቅሎ በማሳደር ጠዋት ላይ ምን እንደተፈጠረ ለማየት የነበረውን ጉጉት የተመለከቱ ወላጆቹም ለሰባት አመት ልደቱ የሶዲየም ሃይድሮኦክሳይድ ናሙና ያለበት ስጦት ያበረክቱለታል።
የሶዲየም ሃይድሮኦክሳይድ እና አሉሚኒየም ውህድ ከፍተኛ ሙቀትና ሃይል እንደሚሰጥም በኦንላይን መረጃዎች በመረዳት ያደረገው ሙከራ ግን በእሳት ሊያይዘው እንደነበርም ይናገራል።
ይህ ለአደጋ ሊያጋልጠው የነበረው ክስተት የወላጆቹ ክትትል እንዲጠናከር ማድረጉን የሚያወሳው ሄማን፥ በልጅነት አይኑ በከባድ ሙቀት የጉልበት ስራ ሲሰሩ የተመለከታቸው ሰዎች ለፈጠራ ስራው መነሻ ሆነውለታል።
የቆዳ ካንሰርን ለመከላከል ስለሚያግዘው “ኢሚኪዩሞድ” የተሰኘ መድሃኒት በስፋት ማጥናቱም የቆዳ ካንሰርን የሚከላከልና በመላው አለም በርካሽ ዋጋ ለገበያ መቅረብ የሚችል ሳሙና እንዲሰራ መራው።
ባለፈው የፈረንጆቹ አመት ጥቅምት ወር ላይም የፈጠራ ስራውን ይዞ በ”3ኤም የወጣት ተመራማሪዎች ውድድር” በመሳተፍ የ25 ሺህ ዶላር ሽልማት ማግኘቱ የሚታወስ ነው።
የተለያዩ የቆዳ ካንሰር በሽታዎችን ለመከላከልና ለማከም ይውላል የተባለው የሄማን በቀለ የሳሙና ፈጠራ መነጋገሪያነቱ ቀጥሎም የታይም መጽሄት በቅርቡ በሚያወጣው የ2024 እትሙ ላይ ትውልደ ኢትዮጵያዊውን ታዳጊ አካቶታል።
የቨርጅኒያ ፌርፋክስ ነዋሪው ሄማን በአሁኑ ወቅት ከጆን ሆፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ የህብረተሰብ ጤና ትምህርትቤት ጋር በመተባበር የቆዳ ካንሰር የሚከላከል ሳሙናውን ውጤታማነት በአይጦች ላይ በመሞከር ላይ ይገኛል።
በቀጣይም የፈጠራ ስራውን የመብት ባለቤትነት ማረጋገጥና በአሜሪካ የምግብና መድሃኒት አስተዳደር እውቅና ማግኘት ይጠባበቃል።
በሚማርበት ውድሰን ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የማርሽ ባንድ አባል የሆነው ሄመን ፍሉት እና ትሮምቦን ይጫወታል፤ ከእኩዮቹ በብዙ እጥፍ የቀደመው ታዳጊው ከንባብ በኋላ ቅርጫት ኳስ እና ቼዝ መጫወት እንደሚያስደስተው ይናገራል።
በታይም መጽሄት እውቅና የተሰጠውና በአዲስ አበባ ተወልዶ በአሜሪካ ያደገው ሄመን በቀለ ማንኛውም ሰው ለታላቅ ስኬት መብቃት እንደሚችል ማሳያ ነው።